ቀጥታ፡

የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ የዝሆኖች መተላለፊያ መስመር መፍትሔ አላገኘም

 አዲስ አበባ (ኢዜአ) መጋቢት 2/2012 በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ምክንያት ችግር ውስጥ የገባው የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ የዝሆኖች መተላለፊያ መስመር ጉዳይ እስካሁን መፍትሔ እንዳላገኘ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

በደቡብ ክልል ቤንች ማጂና ካፋ ዞኖች የሚገኘው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ያስገነባው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሦስት የስኳር ፋብሪካ ጥቅምት 4 ቀን 2011 ዓ.ም ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።

ፋብሪካው በሚገኝበት "ሙይ" አካባቢ 130 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የዝሆኖች መተላለፊያ መስመር ይገኛል።  

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይግዛው ለስኳር ፋብሪካው ለሸንኮራ አገዳ ልማት በሚፈልገው 5 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በተደረገው ቁፋሮ የዝሆኖች መተላለፊያ መስመሩ መዘጋቱን ገልጸዋል።

ለሸንኮራ አገዳ ልማቱ ከተደረገው ቁፋሮ የወጣው አፈር ተቆልሎ በመቀመጡ እናት ዝሆኖች ከልጆቻቸው ጋር መገናኛት እንዳልቻሉ አስረድተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) እ.አ.አ በ1980 ፓርኩ የሚገኝበትን የታችኛው ኦሞ ሸለቆን በሚዳሰስ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቦ ይገኛል።

"የታችኛው ኦሞ ሸለቆ በዩኔስኮ መመዝገቡን ተከትሎ የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ዓለም አቀፍ ጥበቃ እየተደረገለት ይገኛል" ብለዋል።

ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የሚመጡ ዝሆኖች ለመጠለል መተላለፊያ መስመሩን ይጠቀሙ እንደነበረና አሁን መተላለፊያው በመዘጋቱ አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውን አስረድተዋል።

አቶ ጌትነት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሦስት የስኳር ፋብሪካን ሲያስገነባ ከባለስልጣኑ ጋር ምንም አይነት ምክክርም ሆነ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምግማና ጥናት ባለማድረጉ ለሸንኮራ አገዳ ልማቱ ሲባል የተፈጥሮ ሀብት የሆነው የዝሆኖች መተላለፊያ መስመር ላይ ጉዳት ደርሷል።

ችግሩን ለመፍታት ከሁለቱም አካላት የተውጣጡና 11 አባላት ያሉት ኮሚቴ በ2011 ዓ.ም ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን አመልክተው፤ "ኮሚቴው ባደረጋቸው ውይይቶች የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከባለስልጣኑ ጋር ሳይመክር ወደሥራ መግባቱን ስህተት እንደሆነ አምኗል" ብለዋል።

ቁፋሮው ከተካሄደበት ቦታ ውጪ ኮርፖሬሽኑ ሌላ ምትክ ቦታ እንዲሰጠው መጠየቁን አቶ ጌትነት ገልጸው፤ መሬት ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በአካባቢው ተተኪ ቦታ እንደማይገኝ ተናግረዋል።

ኮሚቴው ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ኮርፖሬሽኑ በጉዳዩ ላይ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማና ጥናት እንዲያካሂድ አቅጣጫ ቢሰጥም እስካሁን ኮርፖሬሽኑ ጥናቱን ስለመጀመሩ የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።

ለሸንኮራ ልማቱ በተደረገው ቁፋሮ የተቆለለውን አፈር ለማንሳትና መሸጋገሪያ ድልድይ ለመስራት ከስምምነት ላይ መደረሱን አስታውሰው እስካሁን የተሰጠ መፍትሔ እንደሌለ አመልክተዋል።

ዩኔስኮ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ጥናት እንዲደረግ ማሳሰቡንም ጠቁመዋል።

የዝሆኖች መተላለፊያ መስመሩ ኢትዮጵያ ካሏት እምቅ የተፈጥሮ ሀብት የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዱ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ፋብሪካው ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጥቅም የሚያስገኝ ቢሆንም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር በተጣጣመ መልኩ መካሄድ እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም በበኩላቸው በኦሞ ኩራዝ የስኳር ፕሮጀክት በቅድሚያ አምስት ፋብሪካዎችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ እንደነበረና ያንን መሰረት አድርጎ  የአካባቢና የማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ መካሄዱን ገልጸዋል።

ወደ ግንባታ ሥራ ከተገባ በኋላ ይገነባሉ ከተባሉት አምስት ፋብሪካዎች አንዱ በመታጠፉ የአካባቢና የማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ በድጋሚ እንዲከለስና እንዲታይ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዝሆን መተላለፊያ መስመሩ አምስት ሺህ ሄክታር መሬት ለኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሦስት ስኳር ፋብሪካ የሸንኮራ ልማት ሥራ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

"ለስኳር ፋብሪካ የሸንኮራ አገዳ ልማት ዋናው ግብአት ነው" ያሉት አቶ ጋሻው፤ የዝሆን መተላለፊያውን በማይጎዳ መልኩ የመሸጋገሪያ ድልድይ ግንባታ ሥራውን ጨምሮ ቦታውን ለማልማት ኮርፖሬሽኑ ሀሳብ ማቅረቡን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ሀሳቡን ካለመቀበል በተጨማሪ በተባለው ቦታ የሸንኮራ አገዳ ልማቱ መካሄድ የለበትም የሚል አቋም መያዙን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም