ዳያስፖራው ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ የጎላ ድርሻ አለው - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ የጎላ ድርሻ አለው
ሀዋሳ መጋቢት 1/2012(ኢዜአ) በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር በማስገባት ኢኮኖሚን የማሳለጥ ተሳትፏቸው የጎላ እንደሆነ ተጠቆመ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያለፉት ስድስት ወራት አፈጻጸሙ ላይ ከባለድርሸ አካላት ጋር በሀዋሳ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንዶሰን ግርማ እንደገለፁት፤ ባለፉት ስድስት ወራት በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ከገባው አራት ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዳያስፖራው ድርሻ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ስምንት ሺሕ ሺህ 807 ዳያስፖራዎች የውጭ ምንዛሪ ተቀማጭ ሂሳብ በመክፈት ከ14 ሚሊዮን ዶላር በላይ መቆጠባቸውን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም 41 ቢሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግበው በንግድና ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ላሳዩ ሁለት ሺህ 570 ዳያስፖራዎች የድጋፍ አገልግሎት መሰጠቱንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
ዳያስፖራዎቹ በህክምና፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ሀገራቸውን በሙያቸው እያገዙ መሆናቸውንም አሮ ወንድወሰን ገልጸዋል።
የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሠላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፤ ባለፉት ስድስት ወራት ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት ፈጥረው ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በተለይ ዳያስፖራው የውጭ ምንዛሪ በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት በመላክና ተቀማጭ ሒሳብ በመክፈት የሚያደርገው ተሳትፎ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
ዳይሬክተሯ እንዳሉት ተቋርጠው የቆዩ የዳያስፖራው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችም ዳግም እንዲጀምሩ ማድረግ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
በውጭ ሀገራትም በቅርብ ወራት የተከናወኑት ዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይ በደቡብ አፍሪካና አረብ ሀገራት የኢትዮጵዊያን መብት ተጠብቆ የሚኖሩበትን እንዲሁም በእስር ያሉና ጥቃት የደረሰባቸው ዜጎች ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ዳያስፖራው በሀገሪቱ በፋይናንስ ተቋማት ላይ መሳተፍ እንዲችሉ የሚያግዝ የህግ ማሻሻያ እንዲደረግም ኤጀንሲው ሁኔታዎች የማመቻቸት ተግባር ማከናወኑንም አመልክተዋል፡፡
በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵውያን የህዳሴው ግድቡን በተመለከተ በገንዘባቸውም ሆነ በዕውቀታቸው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚስችል የማነቃቂያ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ እየተደረገ እንደሚገኝም ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡
ከኤጀንሲው ጋር ጠንካራ ቅንጅት ፈጥረው እየሰሩ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳያስፖራ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ለማ ዋቃዮ ናቸው።
"ዳያስፖራዎችን የተመለከቱ ሥራዎችን የምናከናውነው በመናበብ ስለሆነ ለኛም ትልቅ እገዛ አለው "ብለዋል፡፡
ባንኩ ለዳያስፖራው ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፍ መክፈቱና በኤጀንሲው ውስጥ ለዳያስፖራው ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል ቢሮ የማመቻቸት ሥራው በግማሽ የበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።