የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 17 አዳዲስ የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን ሊከፍት ነው

ሶዶ ሰኔ 22/2010 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በቀጣዩ ዓመት 17 አዳዲስ የድህረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞችን እንደሚከፍት አስታወቀ፡፡ ለሚከፈቱ ፕሮግራሞች  የስርዓተ ትምህርት ቀረጻ የሚገመግም መድረክ ትናንት በዩኒቨርሲቲው ተካሂዷል፡፡ የዩኒቨርሲቲዉ የድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር ፋኑኤል ላዕከማሪያም በመድረኩ እንደገለጹት ከሚከፈቱት የትምህርት ፕሮግራሞች ውስጥ ሁለት በሶስተኛ ዲግሪ ሲሆን ቀሪዎቹ በሁለተኛ  ዲግሪ ደረጃ ነው፡፡ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ከሚሰጡት መካከል የአፈር ሳይንስ፣ የዕጽዋት በሽታ ጥናትና የግብርና ምጣኔ ጥናትን ፣ ቋንቋና ኮሙዩኒኬሽን  ይገኙበታል፡፡ መካኒካል፣ ኤሌክትሪካል፣ ሲቪልና ውሃ እንዲሁም የግንባታ ቴክኖሎጂ አስተዳደር በምህንድስናዉ ዘርፍ የተካተቱ ሲሆኑ በተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ባዮሎጂና ስፖርት ሳይንስ ሌሎቹ የትምህርት ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ በሶስኛ ዲግሪ ፕሮግራም ደግሞ በትምህርትና ስነ ባህሪ ዘርፍ፣ በትምህርት አመራር ፖሊሲና በተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ዘርፍ በእንስሳት ህይወትና ስነ ምህዳር ጥበቃ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ዶክተር ፋኑኤል አስታውቀዋል፡፡ የፕሮግራሞቹ ተፈላጊነት ከሃገራዊ ዕድገትና ገበያ አንጻር ሰፊ የዳሰሳ ጥናት እንደተካሄዳበቸው ጠቅሰው "የስርዓተ ትምህርት ቀረጻና ዝግጅት መገምገሙ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል "ብለዋል፡፡ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ 150 እና በሶስተኛ ዲግሪ ደግሞ   አስር ተማሪዎችን በመቀበል በቀጣቱ የትምህርት ዘመን ማስተማር እንደሚጅመሩ አስረድተዋል፡፡ በዘርፎቶ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት ችግርን ለማቃለል ፕሮግራሞቹን ለመክፈት እንዳነሳሳቸው የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲዉ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕረዝዳንት ዶክተር ወንድሙ ወልዴ ናቸዉ፡፡ ፕሮግራሞቹን በጥራት ለማከናወን የሚያግዙ ቤተ ሙከራ ግብአቶችንና የሰው ኃይል የማሟላት ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከቀን መርሃ ግብር ባሻገር በዕረፍት ቀናትና በክረምት መስጠት በሚያስችል መልኩ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው " ለተግባር ልምምድ የሚሆን አደረጃጀት በመፍጠር ተጨማሪ አገልግሎት ለማህበረሰቡ የማቅረብ ተግባር ይከናወናል "ብለዋል፡፡ ከቢሾፍቱ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የስርዓተ ትምህርት ቀረጻውን ለመገምገም የመጡት ዶክተር ፍስሃ ደግሰው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ አዳዲስ ዘርፎችን መክፈት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ "አዳዲሶቹ ፕሮግራሞች ሃገሪቱ ያቀደቻቸውን የዕድገት መስመሮች ለማፋጠንና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚረዱ ናቸው" ብለዋል፡፡ የምህንድስናና ማኑፋክቸርንግ ዘርፍ በዘመናዊ መልኩ የተደራጀ የቤተ ሙከራ ቁሳቁሶችና በተግባር የሚሞክሩባቸዉ ማሳያዎች በስፋት እንደሚፈልጉ ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ ያለበት ደረጃ በቂ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአፈር ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሴር ይኸነው ገብረስላሴ በበኩላቸው አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የአፈር መከላት፣ አሲዳማነት የሚታይበትና በስምጥ ሸለቆ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በጨዋማነት የመጠቃት ችግሩን ለመከላከል ዩኒቨርሲቲው የአፈር ሳይንስ መጀመሩ ጥናቶችን በማካሄድና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በመጠቆም የጎላ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል፡፡ ለሚከፍቱት አዳዲስ የትምህር ፕሮግራሞች የተቀረጸው ስርዓተ ትምህርት ለመገምገም በተዘጋጀው መድረክ ከሀገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ ምሁራን ተሳትፈዋል፡፡ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከ54 በላይ በሆኑ ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም