ከኮሮናሻይረስ ጋር የሚቀራረብ ምልክት ያሳዩ አምስት ሰዎች ውጤት እየተጠበቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከኮሮናሻይረስ ጋር የሚቀራረብ ምልክት ያሳዩ አምስት ሰዎች ውጤት እየተጠበቀ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) መጋቢት 2/2012 ከኮሮናሻይረስ ጋር የሚቀራረብ ምልክት ያሳዩ አምስት ሰዎች በለይቶ ማቆያ ሆነው የምርመራ ውጤት እየተጠበቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ 19) ቅድመ መከላከልን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ እንደገለጹት፤ ከበሽታው ጋር የተቀራረበ ምልክት የታየባቸው ሦስት ኢትዮጵያውያንና ሁለት ቻይናውያን ናቸው።
ሆኖም ''በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዘ ሰው የለም'' ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል፣ ከዓለም ጤና ድርጅትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በትብብር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
''በሽታው እየተስፋፋ በመሆኑ የቁጥጥር ስራውም እየተጠናከረ መጥቷል'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያና በየብስ የሚገቡ መንገደኞች የሙቀት ልየታ ሥራ እየተካሄደ ከ521 ሺህ በላይ ሰዎች በሙቀት ልየታ ምርመራ ውስጥ እንዳለፉ ገልጸዋል።
ከነዚህም 7 ሺህ 100 የሚሆኑት በሽታው ከተከሰተባቸው አገሮች መምጣታቸውን አስታውቀዋል።
እንደ ዶክተር ኤባ ገለጻ፤ በሽታው ከተከሰተባቸው አገሮች የመጡ 1 ሺህ 224 ሰዎች በለይቶ ማቆያ ለ14 ቀናት የተደረገላቸውን ክትትል አጠናቀዋል።
በአሁን ወቅት 974 ሰዎች በክትትል ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ 54 ሰዎች የበሽታውን ተመሳሳይ ምልክቶች በማሳየታቸው በለይቶ ማቆያ ጣቢያዎች መግባታቸውን ተናግረዋል።
''ከነዚህም 49 ሰዎች በተደረገላቸው ምርመራ ከቫይረሱ ነጻ በመሆናቸው ወደ ማኀበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርገዋል'' ብለዋል።
በሽታው በበርካታ አገሮች መስፋፋቱን ተከትሎም ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በተለይ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በ170 ባለሙያዎች በሦስት ፈረቃዎች የሙቀት ልየታ ሥራ እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ በየብስ የሚገቡትን ለመመርመር ደግሞ 30 መግቢያ በሮች ላይ ልየታው በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ተጓዦች ለቡ ላይ የሙቀት ልየታ ሥራ ለመጀመር ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ እንደሆነ አመልክተዋል።
በሽታው ቢከሰት የኮተቤ የካ ሆስፒታልን ለመጠቀም ዝግጅቱ መጠናቀቁን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
ዶክተር ኤባ እንደሚሉት፤ ቫይረሱን ለመከላከል ለ366 የጤና ባለሙያዎች፣ ለ2 ሺህ 500 የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ሆቴሎችና መሰል ተቋማት ሠራተኞች ስልጠና ተሰጥቷል።
ኮቪድ 19 በቻይና በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም፣ በአውሮፓና በአፍሪካ ግን እየተስፋፋ መጥቷል።
በተለይ ጣልያን የሚገኙ 10 ሺህ ሰዎች በበሽታው ሲጠቁ፣ ስፔን፣ ጀርመንና ፈረንሳይን ቫይረሱ አዳርሷል።
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየውም ቫይረሱ 110 አገሮችን ያዳረሰ ሲሆን፣ ከ113 ሺህ በላይ ሰዎች ተይዘዋል።
ከተያዙት ውስጥም 4 ሺህ የሚሆኑት ለህልፈት ሲዳረጉ፣ የበሽታው የስርጭት መጠን ከሰባት በመቶ ከነበረበት ወደ 32 በመቶ ከፍ ብሏል።