ቀጥታ፡

የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ሊጀመር ነው

ሰመራ (ኢዜአ) መጋቢት 2/2012 የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
በኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ለሊሴ ነሜ የሚመራ የልዑኳን ቡድን ከአፋር ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ግንባታው በሚጀመርበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ለሊሴ ነሜ እንደተናገሩት፤ የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ስራ ሲገባ ለሰመራ ከተማ ብሎም ለክልሉ ሁለንተናዊ እድገት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።

ለፓርኩ የሚያስልፈጉ ሼዶች (ቤቶች) ግንባታ ለማስጀመር የተቋራጭ ልየታ  ሥራ  መጠናቀቁን ጠቁመው፤ በቀጣዩ ሳምንት የግንባታ ሥራው እንደሚጀመር  አስታውቀዋል።
በግንባታው ሂደት ከ300 ለሚልቁ ሰዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
ግንባታው ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ባለው ሲሲሲሲ (CCCC) በተባለ የቻይና የኮንስትራክሽን ካምፓኒ እንደሚካሄድ ያስረዱት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ሥራውንም በቀጣዩቹ ስድስት ወራት ጊዜ ለማጠናቀቅም አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንደተሠሩም ገልጸዋል።

የሥራ ተቋራጩ ካምፓኒ  በሀገር ውስጥ የመቀሌና ደብረ-ብርሃን ኢንዱስርትሪ ፓርኮችን መገንባቱም ተመልክቷል።
የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ  በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት "ፓርኩ ወደሥራ ሲገባ የሀገር ውስጥና የውጭ  ባለሃብቶችን ወደ ክልሉ በቀላሉ በመሳብ በክልሉ ለሚገኙ ወጣቶች  ሰፊ የሥራ እድልና የቴክኖሎጂ ሽግግር ይፈጥራል"ብለዋል።
ይህን እድል በአግባቡ ለመጠቀም ክልሉ ካሉት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እና ከሰመራ ዩንቨርሲቲ ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት ወጣቶችን በተለያየ ሙያ መስክ እያሰለጠኑ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ፓርኮ በፍጥነት ወደስራ ለማስገባት  በክልሉ በኩል  አስፈላጊውን የመሰረተ-ልማትና ተጓዳኝ መገልገያዎች እንደሚያመቻች አስታውቀዋል።
የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሰኔ 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የልዑኳን ቡድን አባላት ከአፋር ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ከተወያዩ በኋላ ፓርኩ የሚገነባበትን ቦታ ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም