በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር ተገቢ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር ተገቢ መሆኑ ተገለጸ
አክሱም ሰኔ 22/2010 በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር መንግስት እያደረገ ያለው ጥረትና ተነሳሽነት ተገቢ መሆኑን በአክሱም ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን ተናገሩ፡፡ ጥረቱ ውጤታማ ሆኖ እንዲዘልቅ ህዝብና ምሁራንን ማሳተፍ አንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ገብረመድህን መዝገበ ለኢዜአ እንደተናገሩት መንግስት በኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም ለማስፈን እያደረገው ያለው ጥረት የሚደገፍ ነው፡፡ "ጉዳዩ ከመንግስት በዘለለ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚመለከት በመሆኑ ውይይቱ ወደ ህብረተሰቡ መውረድ አለበት"ብለዋል፡፡ በተለይም ድንበር አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታ ከህይወታቸው ጋር የተያያዘ በመሆኑ በአፈጻጸሙ ላይ እነሱንም ማካተት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ የኤርትራ የልኡካን ቡድን በተደረገላቸው የሰላም ጥሪ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ምሁሩ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት እንግዶች በመቀበል እና ስደተኞች በማስተናገድ ባለፉት ዓመታት ያሳየው ተግባር ለሁለቱም ህዝቦች ሰላም እና እርቅ ያለው ዝግጁነት አመላካች ነው፡፡ " በኢትዮጵያና ኤርትራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ምንም ችግር አልነበረውም " ያሉት ደግሞ በዩኒቨርስቲው የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ገብረህይወት ኃይለማርያም ናቸው፡፡ ሻክሮ የቆየው ግንኙነት መፍታት የሚችሉት በሁለቱ መንግስታት መሆኑን ተናግረው የመንግስታቱ መልካም ግንኙነት ለሁለቱም ህዝቦች ሰላማዊና ወንድማዊ ጉርብትና አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሁን በመንግስታቱ መካከል እየተደረገ ያለው ጥረት ጥሩ ጅምር እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ የሁለቱም መንግስታት ስምምነት ብቻ ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንደማይቻል ያመለከቱት ምሁሩ "መንግስት አሁን የጀመረው መልካም ጥረት በህዝብ ተሳትፎ መደገፍ አለበት" ብለዋል፡፡