በአሶሳ በሙስና ወንጀል የተከሰሱ እስከ 16 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው

አሶሳ መጋቢት 1/2012(ኢዜአ) የአሶሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተለያዩ የሙስና ወንጀሎች የተከሰሱ ሶስት ግለሰቦችን እስከ 16 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ገንዘብ እንዲቀጡ መወሰኑን አስታወቀ።

ፍርድ ቤት ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጸው የቅጣት ውሳኔው የተላለፈው  አንደኛው ተከሳሽ ደግም መኮንን  የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ወረዳ ሁለት  ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፣ ሁለተኛው  አመንቴ ዋቅጅራ

ረዳት ገንዘብ ያዥ እና ሶስተኛው ደግሞ  አሸናፊ በሪሁን ሂሳብ ሠራተኛ ሆነው ሲሰሩ በነበሩት  ላይ ነው።

ግለሰቦቹ በ2010 ዓ.ም. የተጣለባቸውን ኃላፊነት አለአግባብ በመጠቀም ሃሰተኛ የስልጠና ሰዓት መቆጣጠሪያ "አቴንዳንስ" እና የውሎ አበል መክፈያ ፎርም በማዘጋጀት ለ230 ግለሰቦች ስልጠና የተሰጠ በማስመሰል ከ206 ሺህ ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው  አውለዋል።

በዚህም ሦስቱ ተከሳሾች በሃሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀት የሙስና ወንጀል ክስ እንደቀረበባቸው ፍርድ ቤቱ ጠቁሟል።

በተጨማሪም ሁለተኛው ተከሳሽ  ሐምሌ 2010 ዓ.ም. በእጁ የነበረውን 532ሺህ 444 ብር በማጉደል በከባድ የሙስና ወንጀል መከሰሱንም ፍርድ ቤቱ አመልክተዋል።

ሶስተኛ ተከሳሽ ደግሞ በእጁ ከያዘው የመንግስት ገንዘብ ውስጥ ከ6ሺህ259 ብር በላይ ለግል ጥቅም በማወል በከባድ የእምነት ማጉደል ወንጀል ጭምር መከሰሱም ተጠቅሷል።

እንደ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ገለፃ ተከሳሾቹ የፈፀሙት የሙስና ወንጀሎች በሰነድና በሰው ማስረጃ ተረጋግጦባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ሲመለከት ከቆየ በኋላ  የካቲት30/2012ዓ.ም.  በዋለው  ችሎት አንደኛው  ተከሳሽ በስምንት ዓመት ፅኑ እስራት ሁለተኛው በሁለት የሙስና ወንጀል ክሶች 16 ዓመት ፅኑ  እስራት እንዲሁም ሶስተኛው  በሀለት የሙስና ክሶች በዘጠኝ ዓመት ፅኑ እሰራት እንዲቀጡ መወሰኑን አስታውቋል።

በተጨማሪም ሁለተኛ ተከሳሽ  60ሺህ ብር እንዲሁም አንደኛውና  ሶስተኛ ተከሳኞች  ደግሞ የ20 ሺህ ብር ቅጣት እንደተጣለባቸው ፍርድ ቤቱ አመልክቷል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም