25 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የጤና ማዕከል ተመረቀ

63
አዲስ አበባ  ሚያዝያ 26/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ለሚ ከተማ 25 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ  የሚያደርግ  የጤና ማዕከል ተመረቀ። ማዕከሉ ትኩረቱን ኤች አይ ቪ/ኤድስ ላይ ካደረገው 'ፔፕፋር' የአሜሪካ የዕርዳታ ድርጅት በተገኘ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት /ዩ ኤስ ኤድ/ የተገነባ ነው። ጤና ማዕከሉ በአካባቢውና አጎራባች የሚገኙ ከ25 ሺህ በላይ የገጠር ነዋሪዎችን በመሰረታዊ ጤና አገልግሎቶች፣ በልጆች ክትባት፣ በወሊድ፣ በኤች አይ ቪ መከላከልና እንክብካቤ አንዲሁም በሌሎች የጤና አገልግሎቶች ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል። የአካባቢው ማህበረሰቦች ለጤና አገልግሎት ሩቅ መንገዶችን በማቋረጥ ይሄዱ እንደነበር ገልጸው፤ ይህን ድካም ለማቃለል የጤና ማዕከል በመገንባቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል። ዩ ኤስ ኤድ እስካሁን 11 የጤና ማዕከላት፣ 10 የመድሃኒት ማስቀመጫ መጋዘኖችና የብሔራዊ የደም ባንክን ባለፉት አስር ዓመታት ገንብቶ ማስረከቡን የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ገልጿል። የጤና ማዕከሉ የሚፈለገውን ማህበረሰባዊ አገልግሎት እንዲሰጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚያስፈልገውና መንግስት ተግባሩን እንዲያከናውን ተጠይቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም