ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል በመጥፋት ላይ ያሉ ቋንቋዎችን ለመታደግ የሚደረገው ጥረት አናሳ ነው ተባለ

ሀዋሳ ፣ መጋቢት 1/2012 ዓ.ም (ኢዜአ)  በደቡብ ክልል በመጥፋት ላይ ያሉ አምስት ቋንቋዎችን ለመታደግ የሚያስችል በቂ ሥራ እየተሰራ አለመሆኑ ተገለፀ፡፡

በደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት የግጭት አፈታት፣ ሠላም ግንባታና ሕገ-መንግስታዊ እሴቶች ጥናት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሞገስ ዳኜ እንደገለፁት በክልሉ ከሚኖሩ 56 ብሔር ብሔረሰቦች መካከል የሙርሌ፣ ብራይሌ ወይንም ኦንጎታ ፣ ባጫና ኩዌጉ እንዲሁም የናኦ ቋንቋ በከፍተኛ ደረጃ የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል፡፡

እነዚህ በደቡብ ኦሞና ካፋ ዞን ሲነገሩ የነበሩና በመጥፋት ላይ የሚገኙ ቋንቋዎች በጣት የሚቆጠሩ ተናጋሪዎች ያሏቸው አልያም የብሔረሰቦቹ አባላት ይኑሩ እንጂ በሕይወት ያሉ የቋንቋው ተናጋሪዎች የጠፉባቸው ናቸው፡፡

በተለይ የሙርሌ ቋንቋ ከጥቂት አመታት በፊት የነበሩ ሁለት የቋንቋው ተናጋሪ አዛውንቶች ሕይወታቸው በማለፉ አሁን ላይ አንድም ተናጋሪ እንደሌለ ነው የገለፁት፡፡

ምክር ቤቱ የሙርሌን ቋንቋና ሰዋሰዋዊ አጠቃቀም አስጠንቶ እንዲሰነድ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

ጥናት እየተካሄደባቸው ያሉ ሌሎች በመጥፋት ላይ የሚገኙ ቋንቋዎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህን ቋንቋዎች ለመታደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በቂ አለመሆናቸውን ነው የገለጹት።

ቋንቋዎችን እንዲያገግሙ የማድረግ ሥራ ብዙ ሂደቶች እንዳሉት የተናገሩት አቶ ሞገስ የብሔረሰቦቹን አባላት፣ የመንግስትንና የባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ነው ያስረዱት፡፡

በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የፎክሎር ጥናትና ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ግርማ ቡኬ እንዳሉት ደግሞ ደረጃቸው ይለያይ እንጂ በርካታ የክልሉ ቋንቋዎች በመጥፋት ሥጋት ውስጥ ናቸው።

በተለይ ከፍተኛ ተናጋሪ ባላቸው ቋንቋዎች የተከበቡ ሁለትና ከዚያ በላይ ልሳናትን የሚናገሩ ብሄረሰብ አባላት ያሉባቸው ቋንቋዎች የሥጋቱ ሰለባ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት፡፡

ቢሮው በስጋት ላይ ያሉ ቋንቋዎችን ሙዳየ ቃላትና ባህላዊ ሥነ-ቃሎች ከነ ፍቺአቸው በድምፅና በህትመት ሰንዶ ማስቀመጥ እንደሆነና እስካሁን 13 ለሚሆኑ ቋንቋዎች ባህላዊ መዝገበ ቃላት ማሳተሙን ተናግረዋል፡፡

በያዝነው ዓመትም ለዘጠኝ ቋንቋዎች ተመሳሳይ መዝገበ ቃላት ለማሳተም ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

እነዚህን ቋንቋዎች ለመታደግ የተሄደበት ርቀት በችግሩ ልክ አይደለም ያሉት አቶ ግርማ ፤ ሥራው ከፍተኛ በጀትና በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል የሚጠይቅ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከሀዋሳ፣ ጂንካ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጉዳዩ ከታችኛው መዋቅር እስከ ፌዴራል መንግስት ድረስ በትኩረት ሊታይ የሚገባው እንደሆነ ገልፀው፤ ራሱን የቻለ የቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ተቋም ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ይህን ማድረግ ካልተቻለ ችግሩ እየሰፋ እንደሚሄድም አመልክተዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም