ቀጥታ፡

ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የያዘችው አቋም ህጋዊ መሰረት የለውም

ነቀምት፣  መጋቢት 1/2012 (ኢዜአ) ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የያዘችው አቋም ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ የመጠቀም መብት የገደበ ነው ሲሉ ምሁራን ተናገሩ።

የወለጋ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር ዶክተር ደረጀ እናው  በሰጡት አስተያየት ግብፅ ከጥንት  ጀምሮ የአባይን ውሃ ከምንጩ  ለመቆጣጠር ባላት ፍላጎት  አሁን ኢትዮጵያ በወንዙ  ለመጠቀም እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ በመቃወም የያዘችው አቋም የሀገራችን በተፈጥሮ ሃብቷ የመጠቀም መብት የገደበ መሆኑን ተናግረዋል።

አሜሪካ በአገራቱ መካከል ገብታ ለግብጽ በማዳላት የያዘችው አቋም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፃረር በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

86 በመቶ የአባይ ውሃ የምታመነጨው ኢትዮጵያ ውሃውን በመገደብ ለሃይል ማመንጫ የመጠቀምና በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ  ኢትዮጵያ የሚገኙ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በመስኖ  በማልማት ህዝቦችዋን የመመገብ ሙሉ መብት እንዳላት ምሁሩ አመልክተዋል።

በዩኒቨርስቲው የህግ ትምህርት ክፍል መምህር ፈይሣ ኦሉማ በበኩላቸው ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ ኢትዮጵያ በውሃው እንዳትጠቀም የያዘችው አቋም ኢፍትሃዊ ያልሆነና የአንድ ሉዓላዊነት አገር መብት የሚፃረር በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቢ ህግ የምዕራብ ችሎት አቃቤ ህግ አቶ ተረፈ ኪቲላ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ እሰከ አሁን ከአባይ ተፋሰስ አገሮች ጋር ግልፀነትን በመፍጠር እየሰራች መሆኑ ተገቢ ነው ብለዋል ።

ኢትዮጵያ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም መርህን ሳትለቅ ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ተጠቃሚ በሚሆኑበት መንገድ ግንባታውን ማጠናቀቅ የግድ በመሆኑ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም