ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የተጋነነ የንብረት ካሳ ክፍያ ጥያቄ ለስራው ፈተና እንደሆነበት አመለከተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የተጋነነ የካሳ ክፍያ ጥያቄ በፕሮጀክቶች የስራ አፈጻጸም ላይ እንቅፋት እንደሆነበት ገለጸ። 

ባለስልጣኑ የሚያስገነባቸው የመንገድ ግንባታዎች አብዛኞቹ በተለያየ ምክንያት ከተያዘላቸው ጊዜ ዘግይተው እንደሚጠናቀቁ ይታወቃል።

በተለይም የመንገድ ግንባታ የሚካሄድባቸው መስመሮች ላይ የሚፈጸመው የካሳ ክፍያ ትክክለኛ ዋጋ ያለመሆንና የተጋነነ የክፍያ ጥያቄ መቅረብ ችግሩን የከፋ እንዳደረገበት ባለስልጣኑ ይገልጻል።

ባለሥልጣኑ በአሁኑ ወቅት በሚያካሂዳቸው ከ150 በላይ ፕሮጀክቶች ከካሳ ክፍያና ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ችግር እንደገጠመውም አመልክቷል።

የባለስልጣኑ የስራ ሃላፊዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ በመገንባት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በሚጠይቁት የካሳ ክፍያ ግንባታቸው በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቅ እያደረገ ነው።

ፕሮጀክቶቹ ካለፉት ዓመታት ጀምረው የተሸጋገሩና 180 ቢሊዮን ብር በጀት እንደተመደበላቸው ያስረዱት ኃላፊዎች፤ ባለፈው ዓመት ብቻ 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካሳ መከፈሉን አስታውሰዋል።

ለፕሮጀክቶቹ በከተማና በወረዳ አስተዳደር አካላት የነጠላ ዋጋ ሲዘጋጅ ረዥም ጊዜ መውሰዱ ሌላው ችግር መሆኑንም የባለስልጣኑ የመንገድ ወሰን ማስከበር ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ አየለ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የነጠላ ዋጋ ክፍያ መጋነንም ለግንባታው መጓተት መንስኤ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ክፍያውን ለማስተካከል ከየአካባቢው አስተዳደር አካላት ጋር የሚደረገው ክርክር የጊዜ ብክነትን ከማስከተሉም በላይ፤ የበጀት ጫና እየፈጠረ መሆኑንም አቶ ደረጀ ገልጸዋል።

የተጋነነ የካሳ ክፍያ ከመጠየቅ አልፎም ክፍያው ተፈጽሞ ሃብት ንብረትን ያለማንሳት ችግር ለግንባታ ሂደት እንቅፋት እንደሆነ አመልክተዋል።

በባለስልጣኑ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና ከፍተኛ አማካሪ አቶ ተፈራ ዋቅሹም በበኩላቸው የካሳ ክፍያ ጥያቄ መጋነን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል።

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የመንገድ ሕገ ወጥ ግንባታ በፕሮጀክት ክልል ውስጥ በማካሄድ ካሳ ለማግኘት የሚደረገው እንቅስቃሴ መባባሱን ተናግረዋል።

''ለመንገድ ግንባታው የሚያስፈልጉ የተፈጥሮ ሃብቶች በነጻ መጠቀም ሲገባ ካሳ ክፍያ እንዲፈጸምባቸው ይደረጋል'' ብለዋል።

በተጨማሪም የካሳ ክፍያ የተከፈለባቸውን ምሶሶዎች በወቅቱ አለመነሳታቸው ለሥራው መጓተት ሌላኛው ምክንያት እንደሆነም አመልክተዋል።

ባለስልጣኑ የመንገድ ልማትን ለማስፋፋት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስታውቀዋል።

መንግሥት ፕሮጀክቶቹን የሚገነባው ሕዝቡን በልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ መሆኑን በመረዳት የድርሻውን እንዲወጣ ባለስልጣኑ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም