ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ ሴቶችን በሁሉም መስኮች ተሳትፏቸውን ለማሳደግ መስራት አለብን አለ

አዳማ ፣ መጋቢት 01/2012 (ኢዜአ) " ሴቶችን በኢኮኖሚ ፣ማህበራዊና ፓለቲካዊ መስኮች ተሳትፏቸውን ለማሳደግ መስራት አለብን" ሲል የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ትምህርት ሚኒስቴር ከክልሎችና ባለ ድርሻ አካላት ጋር አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ አክብሯል።

በሚኒስቴሩ የመምህራን ትምህርት አመራርና ልማት  ዳይሬክተር ወይዘሮ አሰፋሽ ተካልኝ በዚህ ወቅት እንደገለፁት በተለይም በሚኒስትሮች ምክር ቤት 50 በመቶ የካቢኔ አባላት ሴት በመሆናቸው አበረታችና ተስፋ ሰጪ ነው።

"አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በየዓመቱ ጠብቀን ከመዘከር ባለፈ ሴቶችን በኢኮኖሚ ፣ማህበራዊና ፓለቲካዊ ተሳትፎ ያላቸውን ሚና ማሳደግ ላይ መስራት አለብን"  ብለዋል።

ከለውጡ ወዲህ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት አንፃር ጥሩ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ የተናገሩት ዳይሬክተሯ በሀገር ጉዳይ ላይ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሴቶችን ማገዝ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተለይ የትምህርት ተሳትፏቸውና የአመራር አቅማቸው እንዲጎለብት በስድስት ክልሎች ሚኒስቴሩ  ጥናት ማካሄዱን ጠቅሰዋል።

ሴቶች በእውቀታቸውና በሙያቸው እንዲያገለግሉ፣  የህፃናት ማቆያ በመንግስታዊ መዋቅር በሚፈለገው መጠን ያለመኖርና እንዲሁም ምቹ የሥራ ሁኔታ ያለመፈጠር በጥናቱ የተለዩ ችግሮች መሆናቸውን አመልክተዋል።

የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ አናሳ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሥርዓተ ፃታ ዳይሬክተር ወይዘሮ የሺሐረግ ነጋሽ ናቸው።

"የማህበረሰቡ አስተሳሰብ አለመለወጥ፣ለሴቶች የሚደረገው የአቅም ግንባታ ስልጠና አናሳ መሆኑ በአመራርና ውሳኔ ሰጪነት ቦታ ሚና እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል "ብለዋል።

በቀጣይነት ሴቶችን ለመደገፍና ለማብቃት የሰው ኃይል ልማትና አቅም ግንባታ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በቢሾፍቱ ከተማ የሴቶች ቀን የተከበረው  "የሴቶችን ደህንነትና መብት በማስከበር የሀገርን ሰላም ማስጠበቅ" በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀ ውይይት  ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም