በሞሪታኒያ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ የኢትዮጵያ ልዑክ እየተሳተፈ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሞሪታኒያ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ የኢትዮጵያ ልዑክ እየተሳተፈ ነው
አዲስ አበባ ሰኔ 22/2010 በኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የተመራ የልዑካን ቡድን፣ በሞሪታኒያ በተጀመረው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ በመሳተፍ ላይ ይገኛል። የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ከመካሄዱ በፊት የሚካሄደው የህብረቱ የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ትናንት በሞሪታኒያ ርዕሰ መዲና ኑዋክቾች ተጀምራል። የስራ አስፈጻሚው ስብስባ ነገ የሚጠናቀቅ ሲሆን እሱን ተከትሎም 31ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ሰኔ 24 እና 25 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳል። በጉባኤው በአህጉሪቱ ሰላም እና ፀጥታ እንዲሁም ነፃ የንግድ ቀጠና ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ስብስባ ሁሉም የህብረቱ አባል አገሮች በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎቻቸው ተወክለው የሚሳተፉበት ሲሆን ስብስባው በመሪዎች ጉባኤ ላይ በሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ ተወያይተው ያጸደቋውን ጉዳዮች ለመሪዎቹ ስብስባ ያቀርባሉ።