ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት የሚከታተሉ አታሼዎችን እየመደበ ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 01/2012 (ኢዜአ) መንግስት በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎችን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚሰሩ አታሼዎችን በተለያዩ አገራት እየመደበ መሆኑን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ከ14 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የስራ ስምምነት ወደተደረሰባቸው አገሮች በኤጀንሲዎች ባህዳዊ መንገድ ተልከዋል።

የስራ ስምሪት የተደረገባቸው አገሮችም ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ ጆርዳንና ኳታር  መሆናቸው ታውቋል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ታዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ዜጎች በህጋዊ መንገድ ለስራ እንዲጓዙ ከኤጀንሲዎቹ ጋር በትብብር እየተሰራ ነው።

በርካታ ኤጀንሲዎች በአገሪቱ ሕግ መሰረት ፍቃድ አግኝተውና ተመዝግበው ሰራተኞችን ወደ ተለያዩ አገራት እየላኩ መሆኑንም ገልፀዋል።


መንግስትም በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎችን መብትና ደህነት ለማስጠበቅ የሚሰሩ አታሼዎችን በተለያዩ አገራት እየመደበ መሆኑን ተናግረዋል።

ህጋዊ ፈቃድ ሳይሰጣቸው በሚንቀሳቀሱ ኤጀንሲዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከህግ ውጭ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ30 በላይ ኤጀንሲዎች እንዲሰረዙ መደረጉን ያስታወሱት አቶ ደረጀ በየአገሩ የሚመደቡ አታሼዎችም ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ 350 ኤጀንሲዎች በአራቱ አገሮች ሰራተኞችን እያሰማሩ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የከተማዋ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የስራ ስምሪት ዳይሬክተር አቶ ጥላዬ አለማየሁ ናቸው።


በተያዘው በጀት አመትም በከተማዋ ከሚገኙ ኤጀንሲዎች መካከል በ50ዎቹ ላይ ድጋፍና ክትትል መደረጉን ተናግረዋል።


በክትትሉ ወቅት ያልተቀጠሩ ሰራተኞች በቢሮ ውስጥ መገኘት፣ ቢሮን ዘግቶ መጥፋት፣ የንግድ ፍቃድ በግልፅ ቦታ ላይ አለማስቀመጥና ሌሎችም ችግሮች መስተዋላቸውን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ800 በላይ ኤጀንሲዎች ህጋዊ ፍቃድ አግኝተው ሰራተኞችን ወደ ተለያዩ አገራት በመላክ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም