ቀጥታ፡

ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ የሚያደርገውን ዝግጅት መጋቢት 6 ይጀምራል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኒጀር አቻው ጋር ለሚያደርገው የአፍሪካ ዋንጫ የደርሶ መልስ የማጣሪያ ጨዋታ ከመጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ልምምድ እንደሚያደርግ ተገለጸ።

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራህቱ ቡድኑ ለሚያደርጋቸው ልምምዶች የተጫዋቾች ጥሪ አድርገዋል።

በጥር ወር 2013 ዓ.ም በካሜሮን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አገሮች በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ከህዳር ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ።

በ12 ምድቦች 48 አገሮች በማጣሪያው ላይ እየተሳተፉ ነው።

በምድብ 11 የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም በኒጀር ጀነራል ሴይኒ ኩቼ ስታዲየም እንዲሁም መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከኒጀር አቻው ጋር የማጣሪያ ጨዋታውን ያደርጋል።

ብሔራዊ ቡድኑ ላለበት ጨዋታ የቡድኑ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራህቱ ለ24 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገዋል።

ከ13 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች 23 ተጫዋቾች ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን ከውጭ አገር ለግብጹ "ምስር ኤል ማክሳ ክለብ" የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ በኢንስትራክተር አብርሃም ጥሪ ተደርጎለታል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለዝግጅት ይረዳው ዘንድ ብሔራዊ ቡድኑ ከመጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ልምምድ እንደሚጀምር ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

ብሔራዊ ቡድኑ ከመጋቢት 6 እስከ 16 ቀን 2012 ዓ.ም ልምምድ እንዲያደርግ መርሃ ግብር መዘጋጀቱንም ገልጿል።

ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች እስከ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ መተላለፉን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።

ብሔራዊ ቡድኑ እስካሁን በምድቡ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች በማዳጋስካር 1 ለ 0 ሲሸነፍ፤ ኮትዲቭዋርን 2 ለ 1 አሸንፏል።

በምድቡ በሦስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በፈረንሳዩ አሰልጣኝ ጂን-ጋይ ዋሌም የሚሰለጥነው የኒጀር ብሔራዊ ቡድን እስካሁን ባደረገው ሁለት ጨዋታ በማዳጋስካር 6 ለ 2፣ በኮትዲቭዋር 1 ለ 0 ተሸንፎ ያለ ምንም ነጥብ የምድቡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።

በየካቲት ወር በወጣው የፊፋ የአገሮች የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ 146ኛ ኒጀር ደግሞ 112ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በምድቡ ሁለቱንም ጨዋታ በማሸነፍ በስድስት ነጥብ የምትመራው ማዳጋስካር ከኮትዲቭዋር ጋር መጋቢት 18 እና 22 ቀን 2012 ዓ.ም የደርሶ መልስ ጨዋታዋን ታደርጋለች።

የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ ታውቋል።

በካሜሮን አስተናጋጅነት በሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 24 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም