ቀጥታ፡

የአፍሪካ ኅብረት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሦስቱ አገራት እንዲስማሙ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1 ቀን 2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ ኅብረት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ያላቸውን አለመግባባት በሥምምነት እንዲፈቱ ጠየቀ።

ኅብረቱ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አጠቃቀም ዙሪያ ያላቸውን አለመግባባት በሥምምነት እንዲፈቱ መጠየቁን በለንደን የሚታተመው አልሻርቅ አልአውሳት ዘግቧል።

ኅብረቱ ሱዳን የገጠማትን የሽግግር ጊዜ የኢኮኖሚ ተግዳሮት እንድትፈታ ዓለም አቀፍ አጋር ደርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቋል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት እንደተናገሩት የናይል ወንዝ የአፍሪካ አገራትና ሕዝቦቿ ሁለንተናዊ ትሥሥር የተገመደበት ነው።

"እኛ እንደ አፍሪካ ኅብረት ወንድሞቻችን የሆኑትን የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ ዜጎችን የምንጠይቀው በጉዳዩ ላይ አስታራቂ ሀሳብ እንዲያመጡ ነው" ብለዋል።

ግብፅና ኢትዮጵያ በግድቡ አሞላልና አጠቃቀም ዙሪያ አለመግባባታቸው የሚታወቅ ሲሆን ኢትዮጵያ ዋሽንግተን ላይ በተደረገው የመጨረሻ ስብሰባ ዝግጅቷን ባለመጨረሷ እንዳልተሳተፈች አሳውቃለች።

በሱዳን የሦስት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት የኅብረቱ ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት የጉብኝታቸው ዓላማ በሱዳን ያለውን የሰላም ሂደት ለመመልከት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም በአገሪቱ ከሚገኙ ብሔራዊ ፖለቲከኞች ጋር ኢኮኖሚውን፣ ፖለቲካውንና በነሐሴ 2011 ዓ.ም የተደረሰውን የሕገ መንግሥት ድንጋጌ አተገባበር በተመለከተ መወያየታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

በተያያዘ ዜና የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት ጋር ተወያይተዋል።

ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ እየተደረገ ያለው ድርድር ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ምክክር አድርገዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት የናይል ወንዝ የሀገራቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ የትብብር መነሻ ሊሆን ይገባል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት በበኩላቸው የሁሉንም አገሮች ሕዝቦች ጥቅም ባማከለ መልኩ ሥምምነት ላይ መደረስ እንዳለበት እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም