ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ባለፈው ዓመት በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ሰለባ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኙ

አዲስ አበባ መጋቢት 1/2012(ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ባለፈው ዓመት በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ሰለባ ቤተሰቦችና ወዳጆች ብርታትና መጽናናትን ተመኙ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአደጋውን አንደኛ ዓመት በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት በአደጋው ሕይወታቸው ያለፉትን ሰዎች አስበዋቸዋል።

በመልእክታቸውም ለሟቾች ቤተሰቦችና ወዳጆች በድጋሚ መጽናናትና ብርታትን እንዲሰጣቸው ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 – 800 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ መላውን ዓለም አሳዝኖ አልፏል።

አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመጓዝ ላይ ሳለ ከስድስት ደቂቃ በኋላ ከበረራ ተቆጣጣሪዎች ጋር ግንኙነቱ ተቋርጦ   ቢሾፍቱ አካባቢ መከስከሱ ይታወሳል።

በአደጋው 8 የበረራ ሠራተኞችን ጨምሮ  9 ኢትዮጵያውያን መንገደኞችና ከ30 በላይ አገራት ዜጎች በጥቅሉ የ157 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ከደረሰው አደጋ ቀደም ብሎ የኢንዶኔዥያ ተመሳሳይ አውሮፕላን 186 መንገደኞችን አሳፍሮ በመጓዝ ላይ እያለ በመከስከሱ መንገደኞቹ በሙሉ ማለቃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም