የጀጎል ግንብ አጥር በሶስት ቦታዎች የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል - ኢዜአ አማርኛ
የጀጎል ግንብ አጥር በሶስት ቦታዎች የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል

ሀረር፣ መጋቢት 1/2012 (ኢዜአ) በአለም ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል ግንብ አጥር እየፈረሰ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ከከፋ ጉዳት እንዲታደገው ነዋሪዎችና በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎች ጠየቁ ።
በሀረር ከተማ የሰንጋ በር ነዋሪ ወይዘሮ ረውዳ መሀመድ በሰጡት አስተያየት “ በሀረሪ ክልል ያለን ቅርስ የጀጎል ግንብና በውስጡ የሚገኙ ታሪካዊ ፣ ሀይማኖታዊና ጥንታዊ የመስህብ ስፍራዎች ዋነኞቹ ቢሆኑም አሁን ግን የግንቡ አጥር የመፈራረስ አደጋ ተጋርጦበታል ነው ያሉት።
በበርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ቱሪስቶች የሚጎበኘው የጀጎል ግንብ አጥር እየፈራረሰ በመሆኑ የፌዴራል መንግስትና በተለይ ደግሞ የክልሉ አመራር ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሊታደጉት እንደሚገባ ገልፀዋል።
በቱሪዝም ዘርፍ የገቢ ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው የጀጎል ግንብ መፈራረስ ከጀመረ ሶስት ዓመታት እንዳለፈው የገለፁት ደግሞ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩት አቶ አብዲ አደም ናቸው።
ለአጥሩ መፍረስ ዋናው ምክንያት በውስጡ አለአግባብ የሚለቀቀው ፍሳሽ ዋናው መሆኑን ተናግረዋል።
አካባቢውን የሚጎበኙ ቱሪስቶች በተደጋጋሚ ለምን ጥገና እንደማይደረግለት ይጠይቃሉ ያሉት አቶ አብዲ ለግንቡም ሆነ በውስጡ ለሚገኙት ታሪካዊ ቤቶች እንክብካቤ የሚያደርግለት አካል አለመኖሩን እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል።
ቅርሶቹን ለትውልድ ለማስተላለፍ ትኩረት ተሰጥቶ ጥገና እንዲደረግለትም ጠይቀዋል።
በአስጎብኚነት የተሰማሩ አቶ ሊሻን ከተማ በበኩላቸው በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት በቅርስነት የተመዘገበው ታሪካዊ ስፍራ ትኩረት እንዳልተሰጠው በጎብኚዎች ጭምር በተደጋጋሚ እየተነሳ መሆኑን ተናግረዋል።
ቅርስነቱን እንዳናጣው መንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
በክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ የቅርስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ነቢል በክሪ እንደተናገሩት የጀጎል ግንብ በእድሜ ብዛትና በውስጡ የሚኖሩ ነዋሪዎች በሚያደርሱበት ጉዳት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሶስት ስፍራዎች ላይ የመፍረስ አደጋ ደርሶበታል።
የጀጎል ግንብ አጥር የመፍረስ አደጋን ለመታደግ 5 ሚሊዮን ብር በመመደብ በጥናት ላይ የተመሰረተ የጥገና ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ግንቡንና በውስጡ የሚገኙ ታሪካዊ ቤቶችን በዘለቄታዊነት ለመታደግ ደግሞ ከፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመቀናጀት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ስራ ለማከናወን የጥናት ስራ ተጠናቅቆ በጀት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከጀጎል አካባቢ በ2 መቶ በላይ የተለያዩ በውስጥ ለውስጥ ቦይዎች የሚወጡ ፈሳሾችን ወጥ በሆነ መንገድ ለማስኬድ ከክልሉ ከተማ ልማት ጋር የጥናት ስራ በመጠናቀቁ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በሐረሪ ክልል በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባውና በዩኔስኮ በአለም ቅርስነትት የተመዘገበው ታሪካዊው የጆጎል ግንብ በውስጡ ጥንታዊ መኖሪያ ቤቶችና አምስቱ መግቢያ በሮች፣ ባህላዊ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ የፈረንሳዊው ባለቅኔ አርተር ራንቡ መኖሪያ ቤት፣ የሐረሪ ብሔረሰብ ሙዚየሞች፣ ቤተክርስትያናትና መስኪዶች ይገኛሉ።