ቀጥታ፡

በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በኮሮና ቫይረስ ተያዙ ከተባሉ ሁለት ኢትዮጵያውያን አንዱ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ ተረጋገጠ

መጋቢት 1/2012 (ኢዜአ) ባለፉት ቀናት በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በኮሮና ቫይረስ ተያዙ ከተባሉ ሁለት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ ተረጋገጠ።

የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፤ በኮረና ቫይረስ ተይዘዋል ተብለው ከተጠረጠሩት ሁለት ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ ነፃ መሆኑ ተረጋግጧል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደተናገሩት፤ ሁለቱም ኢትዮጵያውያን ነዋሪነታቸውን በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ያደረጉ መሆናቸውን በማረጋገጥ አንደኛው ግለሰብ በንጉሱ የግል አውሮፕላን ውስጥ የሚሰራ የበረራ ባለሙያ መሆኑን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

“ከሁለቱ ኢትዮጵያውያን መካከል አንደኛው ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ መረጋገጡን ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጤና ሚኒስቴር አረጋግጠናል፤ ሁለተኛው ታማሚ ግን በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ዝርዝር መረጃ አልሰጡንም። ነገር ግን አሳሳቢ የሚባል ነገር እንዳልሆነ ገልጸውልናል''። ሲሉ ዶክተር ሊያ ታደሰ አብራርተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ የአንደኛው ኢትዮጵያዊ ሁኔታ ከባድ የሚባል አይደለም ማለታቸውን ሲያብራሩ “በሽታው ልክ እንደ ጉንፋን አይነት በሽታ እንደመሆኑ አብዛኛዎቹ ታማሚዎች ልክ እንደማንኛውም ጉንፋን ታማሚ ነው የሚሆኑት።ነገር ግን አንዳንዶች በሽታው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያድግባቸዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያዊው ጉንፋን ብቻ በሚባል ደረጃ ላይ ነው ያለው ማለት ነው'' ብለዋል።

ስለሆነም አንደኛው ኢትዮጵያዊ ከህመሙ የማገገም እድል እንዳለው ሚኒስትር ዴኤታዋ አስረድተዋል።

ከቫይረሱ ነጻ እንደሆነ የተነገረው ግለሰብ ግን በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲሆን የሚያስገድደው ነገር እንደሌለና ወደ ቀድሞ ህይወቱ መመለስ እንደሚችልም ታውቋል ሲሉ አክለዋል።

ከግለሰቦቹ ማንነት ጋር በተያያዘ አንደኛው ኢትዮጵያዊ የአየር መንገድ ሰራተኛ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን፤ሁለተኛው ግን ኢትዮጵያዊ ከመሆኑ ውጪ ሌላ መረጃ አለማግኘታቸውንም ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ 93 አገራት ቫይረሱ እንደተገኘ መገለጹን ተከትሎ ምናልባት በእነዚህ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለበሽታው ተጋልጠው እንደሆነ ተጠይቀው፤ ከበሽታው ጋር በተያያዘ እስካሁን ከየትኛውም ኤምባሲ መረጃ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም