ቀጥታ፡

በሁመራ በኩል ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ31 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ

ሁመራ፣የካቲት 30/2012 (ኢዜአ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ስድስት ወራት በሁመራ በኩል ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ31 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገለጸ። 

 በኢትዮጰያ ጉምሩክ ኮሚሽን የሁመራ ቅርጫፍ  የውጭ እቃዎች አወጣጥ ቡድን አስተባባሪ አቶ ሐድጉ አምበስ ጽህፈት ቤት እንዳሉት ከተላኩት የግብርና ምርቶች መካከል ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማቅመም፣ ማርና ቅቤ ይገኙበታል።

የምርቱም መጠን 187 ሺህ ኩንታል እንደሆነ አመልክተው ሱዳን፣ እስራኤል፣ ቻይናና የአውሮፓ ሀገራት  ምርቶቹ ከተላኩባቸው ሃገራት ውስጥ  የጠቀሷቸው ናቸው።

የምርት አቅርቦቱ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ100ሺህ ኩንታል መቀነሱንና ገቢውም በ13 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያነሰ መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል።

ገቢው የቀነሰው ወደ ሃገራቱ የተላከው የሰሊጥ ምርት መጠን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ እንደሆነ አመልክተዋል። 

በአካባቢው የሰሊጥ ነጋዴዎች መካከል አቶ ተስፋዬ ወልደምህረት በሰጡት አስተያየት ሰሊጥ  ባለፈው ታህሳስ ወር ኩንታሉን እስከ አራት ሺህ 500 ብር ድረስ የገዙበት ዋጋ ወደ አራት ሺህ200 ብር መውረዱን ገልጸዋል።

አምና የሰሊጥ ምርት ዋጋ የተሻለ ስለነበር በግማሽ የበጀት ዓመቱ እስከ አንድ ሺህ ኩንታል ድረስ ለውጭ ገበያ ማቅረባቸውን አስታወሰዋል።

"ዘንድሮ ግን በሰሊጥ ዋጋ መውረድ ምክንያት 400 ኩንታል ለመግዛትም የኪሳራ ስጋት አድሮብኛል "ብለዋል።

 ሌላው  ሰሊጥ አቅራቢ  አቶ ፍሳሃ ፀሐዬ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የሰሊጥ ዋጋ ከጎረቤት  ሱዳን ጋር ሲነፃፀር  ቅናሽ እንዳለው ተናግረዋል። 

በዚህም ምክንያት በ2011 በጀት ዓመት ሦስት ሺህ ኩንታል ሰሊጥ አቅርበው እንደነበር አስታውሰው  ዘንድሮ ግን ዋጋው በመዋዠቁ አንድ ሺህ ኩንታል የሰሊጥ ምርት ብቻ ወደ ውጭ መላካቸውን ጠቅሰዋል። 

በሁመራ የሰሊጥ ምርት በማቅረብ የተሰማሩ ነጋዴዎች የንግድና ኢንዲስትሪ ሚኒስቴር የሰሊጥ ዋጋ ተመን ማስቀመጡ ለኪሰራ እየዳረጋቸው መሆኑን ከሁለት ወራት በፊት  ኢዜአ ዘግቦ ነበር።

በንግድና ኢንዱስትሪ  ሚኒስቴር የሰብል ምርት ዳይሬክተር አቶ መስፍን አበበ  በወቅቱ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ  ባለፈው ዓመት የነበረው የሰሊጥ የሀገር ውስጥ ዋጋ የተጋነነ እንደነበር  ገልጸዋል።

በሰሊጥ የውጭ ንግድ ስራ የተሰማሩም ሰሊጥ በተጋነነ ዋጋ እየገዙ በዓለም ገበያ  በዝቅተኛ ዋጋ እንደሚሸጡ  አመልክተዋል።

ይህም ነጋዴዎች ባገኙት የውጭ ምንዛሪ ተጠቅመው በርካታ የውጭ እቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት እንደሚሸጡና ይህን ለማስተካከል ሚኒስቴሩ አዲስ አሰራር ተግባራዊ ማድረጉን ዳይሬክተሩ በወቅቱ ገልጸው ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም