በአዲስ አበባ የተካሄደው ኤግዚቢሽን የፈጠራ ውጤቶቻቸውን ይዘው ለቀረቡ የማስተዋወቂያ መድረክ እንደነበር ተገለጸ

130

አዳዲስ አበባ፣ የካቲት 30/2012(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ውጤቶች ኤግዚቢሽን የፈጠራቸውን ይዘው ለቀረቡ ጥሩ የማስተዋወቂያ መድረክ እንደነበር ተገለጸ።

የመዲናዋ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት የቴክኒክና ሙያ የትምህርትና ሥልጠና ሳምንቱ ሥራዎቻቸውን ለሕዝብ ለማስተዋወቅ እንዳስቻላቸው ተናገሩ።

የኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኤግዚቢሽኑ ሥራዎቻቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ ሆኗቸዋል።

ሥራዎቻቸውን ለማሻሻል ያስቻል ግብዓትም እንዳገኙበትም ገልጸዋል።

ከእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የኤሌክትሮኒክስ ዲፓርትመንት ተማሪ ኢዮብ ብርሃኑ በፈጠራ ያበረከተው ከሌባ የሚከላከል ቦርሳ የገበያ ትስስር ውስጥ ለመግባት ዕድል እንደሚፈጥርለት እምነቱን ገልጿል።

ከተመልካቾች ባገኘው አስተያየት ታግዞ ሥራውን እንደሚያሻሽለውም ተናግሯል።

የአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኝ ሳሙኤል ኃይለማርያም ያቀረቡት አትክልትን ከአፈር ውጪ በማሳደግና ሰው ሰራሽ በሆነ ገንዳ ውስጥ ዓሣን የማርባት ዘዴ ተቀባይነት በማግኘቱ ለሌሎች ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።

''የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ ለማግኘትና ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለኢንተርፕራይዞች ለማስተላለፍ ኤግዚቢሽኑ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል'' ያሉት ደግሞ የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ አስተባባሪ አቶ እንዳለ ትዕዛዙ ናቸው።

የአዲስ አበባ የቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንና ቴክኖሎጂ ሽግግር  

ዳይሬክተር አቶ በላይ ከፈለ በኤግዚቢሽኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መቅረባቸው ለኢንዱስትሪዎችና ለኢንተርፕራይዞች ቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር አስችሏል።

የኅብረተሰቡም ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚረዳም ተናግረዋል።

"ፈጠራ ቀስ ብሎ የሚመጣ ነው" ያሉት አቶ በላይ፤ ሌሎች አገሮች የፈጠሩትን ቴክኖሎጂ በመቅዳት ከአገሪቱ ነበራዊ ሁኔታ ጋር በማቀናጀት ለእይታ መቅረባቸው ለኢንዱስትሪ ሽግግር መሠረት ይሆናል ብለዋል።

በኤግዚቢሽኑ የከተማዋ የመንግሥትና የግል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተሳትፈዋል።

ኤግዝቢሽኑ ላለፉት አራት ቀናት የተካሄደው "ቴክኒክና ሙያ የወጣቶች የስኬት በር" በሚል መሪ ሃሳብ ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም