ቀጥታ፡

የመዲናዋ አሽከርካሪዎች በቤንዝን እጥረት ለእንግልት ተዳርገናል አሉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30/2012(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ባለፉት ሦስት ቀናት ባጋጠመው የቤንዝን እጥረት ለእንግልት መዳረጋቸውን አሽከርካሪዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በበኩሉ በአገሪቱ ምንም አይነት የነዳጅ እጥረት የለም፤ ማደያዎቹ የፈጠሩት ነው ብሏል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎቹ ባለፉት ሦስት ቀናት ነዳጅ ለመቅዳት ወደ ማደያዎች ሲሄዱ "ቤንዝን አልቋል" የሚል ምላሽ እየተሰጣቸው መሆኑን ነው የገለጹት።

አቶ መንግስቱ በልሁ "ምክንያቱን ባላወቅነው ሁኔታ እስከ ምሽቱ አራት ሠዓት ድረስ ረጅም ሰልፍ ታግሰን ነው ነዳጅ እየቀዳን ያለነው" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

"በመዲናዋ የተለያዩ የነዳጅ ማደያዎች የሚታየውን ረጃጅም ሰልፍ ተከትሎ ነዳጅ ሊጠፋ ነው የሚል ወሬ መናፈሱ ሁሉንም ነዳጅ ፈላጊ ከማድረግ ባለፈ ችግሩን አባብሶታል" ያሉት ደግሞ አቶ ሱራፌል በእምነት ናቸው።

ነዳጅ ለመቅዳት ከትናንት በስቲያ ከአንድ ሠዓት በላይ ተሰልፈው 'ቤንዝን አልቋል' በመባላቸው ትናንትና በድጋሚ ከአንድ ሠዓት በላይ ተሰልፈው ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

"መንግስት የነዳጅ እጥረት በሚያጋጥምበት ጊዜ አስቀድሞ ሊያሳውቅ ይገባል" ነው ያሉ አቶ ሱራፌል።

ሰሞኑን በመዲናዋ በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች እየታየ ያለውን የተሽከርካሪዎች ሰልፍ አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ኃይለማርያም በአገሪቷ ምንም አይነት የነዳጅ እጥረት አለመኖሩን ገልጸዋል።

ችግሩ በየወሩ መጨረሻ የሚደረግን የነዳጅ ዋጋ ተመን ማሻሻያ ተከትሎ ማደያዎች የገንዘብ ጭማሪ ይኖራል በሚል እሳቤ በራሳቸው የፈጠሩት መሆኑን ተናግረዋል።

"በመላ አገሪቷ በቀን 2 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ያስፈልጋል" ያሉት አቶ ታደሰ ድርጅቱ ከፍላጎቱ ጋር ተመጣጣኝ ነዳጅ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የነዳጅ አስፈጻሚ አካላት ኃላፊነታቸውን በሚገባ እየተወጡ ባለመሆኑ የነዳጅ እጥረቱ የሚከሰትበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም