የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለአካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች 120 መኖሪያ ቤቶችን አስገነባ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለአካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች 120 መኖሪያ ቤቶችን አስገነባ
ጎንደር፣የካቲት 30/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በግጭት ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ የአካል ጉዳተኞችና ለአቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች 120 የመኖሪያ ቤቶች ማስገንባቱን ገለፀ።
በማህበሩ የጎንደር ቅርንጫፍ ሃላፊ አቶ አታለል ታረቀኝ ለኢዜአ እንደገለጹት ማህበሩ ቤቶቹን ያስገነባው በማእከላዊና ምእራብ ጎንደር ዞኖች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የመኖሪያ ቤታቸው ለወደመባቸው አቅመ ደካሞች ነው።
በዚህም ባለፈው ዓመት በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ቤት አልባ የሆኑ 120 አባወሯዎችን በስራቸው ከሚተዳደሩ 720 ቤተሰቦቻቸው ጋር ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
በሁለቱ ዞኖች ለተገነቡት የቆርቆሮ ቤቶችም ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን አመልክተዋል።
የተገነቡት የመኖሪያ ቤቶች በግጭት ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው እስከ አሁን በዘመድና በግለሰቦች ቤት ተጠልለው የሚገኙትን አቅመ ደካሞችና የአካል ጉዳተኞች በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው።
ሰሞኑንበማእከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ የተገነቡትን 60 ቤቶች የማስረከብ ስራ የተጀመረ ሲሆን በቀጣይም በምእራብ ጎንደር ዞን የተገነቡ ቀሪ ቤቶችን የማስረከብ ስራ ይከናወናል ብለዋል።
ማህበሩ በሁለቱ ዞኖች ተፈናቅለው በመጠለያ ለነበሩ አባወሯና ቤተሰቦቻቸው የምግብ፣ የአልባሳትና የቤት ቁሳቁስ በማቅረብ ሰብአዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል።
የማእከላዊ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ መብራቱ ደጉ እንዳሉት የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ቦታቸው ለመመለስ ባለድርሻ አካላት ጥረት እያደረጉ ነው።
የቀይ መስቀል ማህበር ባስገነባቸው ቤቶች ተጠቃሚ የሚሆኑ ተፈናቃዮችን በመመልመል የማስረከብ ስራ በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በዞኑ በተነሳው ግጭት ከተቃጠሉት አጠቃላይ 3 ሺህ 887 መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በማህበሩ የተገነቡትን ሳይጨምር 3 ሺህ 700 የሚጠጉ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ተላልፈዋል።
በመጠለያ የቆዩ ከ40 ሺህ በላይ አባወሯና ቤተሰቦቻቸው ወደ ቀያቸው ተመልሰው የተረጋጋ ሕይወት በመምራት ላይ እንደሚገኙ ተመልክቷል።