ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለሴቶች አመራር ሰጪነት የሰጠችውን ትኩረት አፍሪካ ልትማርበት ይገባል

አዲስ አበባ ፣  የካቲት 30/2012 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለሴቶች አመራር ሰጪነት የሰጠችውን ትኩረት አፍሪካ ልትማርበት እንደሚገባ የዓለም አቀፍና የአህጉራዊ ተቋማት ኃላፊዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ ከካቢኔዋ ከፊሉን በሴቶች እንዲመራ ማድረጓ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት የሴቶች መርሐ ግብርና የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች ለኢዜአ እንዳስረዱት አገሪቷ ሴቶችን ወደ አመራርነት በማምጣት በአህጉሪቱ ግንባር ቀደም ከሚባሉት መካከል ተሰልፋለች።

የመርሐ ግብሩ ተወካይ ማርጋሬት ኢንደዋዮ የኢትዮጵያ መንግሥት የሴቶችን አመራር ሰጪነት ማሳደጉ አፍሪካ ልትማርበት የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ይህም ሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴያቸው እንዲሰፋ ያደርጋል በማለትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የሴቶችን የአመራርና የውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማጎልበት ከወንዶችም ጋር መሥራት እንደሚያስፈልግም  አመልክተዋል።

ሁሉም የአፍሪካ አገራት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ተመሳሳይ ውሳኔ በማሳለፍ ሴቶችን ለአመራርነት ያበቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

"አመራር ሰጪነት ማለት ፕሬዚዳንት ወይም ሚኒስትር መሆን ብቻ አይደለም" ያሉት ተወካይዋ ፤ ድርጅታቸው ሴቶች በሙያቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያበረታታ ገልጸዋል።

በተለይም በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ብቁና በኢኮኖሚም የድርሻቸውን ተወጥተው አገርን ማሳደግ የሚፈልጉ ሴቶችን በብዛት ለማፍራት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመሥራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የሴቶች ስርዓተ-ጾታና የልማት ጊዜያዊ ዳይሬክተር ሌሃዉ ቪክቶሪያ ማሎካ የኢትዮጵያ መንግሥት የሴቶችን የአመራር ሰጪነት ሚና ለማሳደግ የወሰደው እርምጃ አፍሪካ ልትማርበት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

የአህጉሪቱን ሴቶች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ተቋቁመው ራሳቸውን በትምህርት በማብቃት በአመራር ሰጪነት ለመሳተፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሴቶች እስከታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል ድረስ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ስምምነት መደረሱንም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

በከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ ሴት አመራሮችና ሌሎች ሴቶችን የሚያበቃ መርሐ ግብር እየተተገበረ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም