ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም ለማስፈን የጀመሩት እንቅስቃሴ በቀጠናው አዎንታዊ ተጽእኖ የሚፈጥር ነው - አንቶኒዮ ጉተሬዝ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም ለማስፈን የጀመሩት እንቅስቃሴ በቀጠናው አዎንታዊ ተጽእኖ የሚፈጥር ነው - አንቶኒዮ ጉተሬዝ
አዲስ አበባ ሰኔ 22/2010 ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም ለማስፈን የጀመሩት እንቅስቃሴ በቀጠናው በጎ የሆነ ተጽእኖ የሚፈጥር መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ገለጹ። የኤርትራ መንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ያደረገው ጉብኝት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማሻሻል የተወሰደ የመጀመሪያ የተግባር ርምጃ እንደሆነ ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል። አገሮቹ ለረጅም ጊዜ የነበረውን አለመግባባትና ውጥረት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የጀመሩት ጥረት በቀጠናው በጎ ተጽእኖ እንደሚኖረው መግለጻቸውን የዋና ጸሀፊው ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ዱጃሪክ አመልክተዋል። ሁለቱ ጎረቤት አገሮች የጀመሩት ዲፕሎማሲያዊ ውይይት ለዘላቂ ሰላም መስፈን ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም አስታውቀዋል። ተመድ በሁለቱ አገሮች መካከል ላለው የድንበር ውሳኔ ተፈጻሚነት፣ ለሰላም ሂደቱ ውጤታማነትና መሰል ጉዳዮች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አስታውቀዋል። የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጉዳዩን አስመልክቶ ከሳምንት በፊት በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያና ኤርትራ በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል የተጀመሩትን በጎ ስራዎች ማድነቃቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የአገሮቹ ግንኙነት እንዲሻሻል ለጀመሩት ስራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የሰላም ጥሪ በመቀበል የኤርትራ መንግስት ልዑካን በዚህ ሳምንት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማደርጋቸው ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በኤርትራ መንግስት ከፍተኛ ልዑካን በኩል ለፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ መልዕክት ልከዋል። አዲስ አበባ ላይ ከኤርትራ መንግስት ከፍተኛ ልዑክ ጋር የተደረገው ውይይት በሁለቱ ሀገራት መካከል ማምጣት ለሚፈለገው ሰላም ምቹ እድል የፈጠረ መሆኑም ተገልጿል። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የሁለትዮሽ ውይይት ሲካሄድ ከ20 ዓመታት በኋላ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ለዓመታት ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እልባት እንዲያገኝና ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው። በተጨማሪም ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑም ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮችና ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በድንበር ጉዳይ ላይ የሚነሱ ጉዳዮችን በውይይትና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት መንግስት እንደሚሰራ ገልጸው ነበር።