ቀጥታ፡

በኮሮና ቫይረስ ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ሆስፒታሎች ተዘጋጅተዋል

አዲስ አበባ የካቲት 30/2012 ( ኢዜአ) በኮሮና ቫይረስ ላይ በልዩ ትኩረት የሚሰሩ ሆስፒታሎችን ማዘጋጀትን ጨምሮ ስርጭቱን ለመቆጣጠር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ቫይረሱን ለመከላከል የተቋቋመው ብሔራዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰው እንደሌለም ኮሚቴው ገልጿል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው 80ኛ መደበኛ ስብሰባ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ብሔራዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴ እንዲቋቋም ወስኖ ኮሚቴው ወደ ስራ ገብቷል።

ብሔራዊ ኮሚቴው በጤና ሚኒስቴር የሚመራ ነው።

ኮሚቴው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እያከናወነ ያለውን ተግባር አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ሪፖርት አቅርቧል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ ኮሮናንቫይረስን ለመከላከል ከተለያዩ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡ 30 በሮች ተለይተው ክትትል እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

ቫይረሱ ድንገት ቢከሰት እንኳ የየካ ኮተቤ ሆስፒታል ለዚሁ ስራ የሚሆን አስፈላጊ ግብዓት አሟልቶ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ እስከ 600 ሰዎችን እንዲያስተናግድ ሆኖ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

የስርጭት መጠኑ ሆስፒታሉ ሊያስተናግደው ከሚችለው ሰው ቁጥር በላይ ከሆነም የቢሾፍቱ መከላከያ ሆስፒታል ዝግጁ ሆኖ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ነው ዶክተር ሊያ ያስረዱት።

ከክልሎች ጋርም ቫይረሱን ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የኮሮናቫይረስ ምርምራ በውጭ አገር ይካሄድ እንደነበር ያወሱት ዶክተር ሊያ አሁን የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምርመራውን በአገር ውስጥ እያካሄደ ነው ብለዋል።

እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዘ ሰው እንደሌለም ገልጸዋል።

የኮሮናቫይረስ /ኮቪድ-19/ ከተከሰተ ጀምሮ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 3 ሺህ 831 የደረሰ ሲሆን 110 ሺህ 99 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።

በቫይረሱ የሞቱ ቻይናዊያን ቁጥር 3 ሺህ 120 ሲሆን በዚሁ ሳቢያ የሞቱ የተለያዩ አገራት ዜጎች ቁጥርም ወደ 711 አሻቅቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም