ቀጥታ፡

የደቡብ ኦሞ ህዝብ የህብረ ብሄራዊና የመደመር መገለጫ ነው... ጠቅላይ ሚንስትር አብይ

 አዲስ አበባ የካቲት 29/2012 ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የደቡብ ኦሞ ህዝብ የህብረ ብሄራዊና የመደመር መገለጫ ተምሳሌት መሆኑን ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ ስታዲየም ለተሰበሰቡት የአካባቢው ህዝብ ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም ደቡብ ኦሞን "ትንሿ ኢትዮጵያ፣ የህብርና የአብሮነት መገለጫ እንዲሁም በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ታላቅ ህዝብ" የሚኖርበት ሲሉ አወድሰዋል።

የኦሞ ሸለቆም ልክ እንደ አፋር ሁሉ በሰው ልጆች የአኗኗር ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑን አንስተዋል።

አካባቢው ታሪካዊና በብዙ ጎብኝዎች የሚዘወተር እንዲሁም የኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊነት አንዱ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።

የደቡብ ኦሞ ህዝብ መደመርን ቀድሞ የተረዳ ከሰው ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋርም የተለያዩ እሴቶችን አካብቶና አሰባስቦ የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ ኦሞ የእርቅና የባህላዊ ዳኝነት ስርአትም ሰፊ ትምህርትና ተሞክሮ የሚቀሰምበት ድንቅ ባህላዊ እሴት መሆኑን አብራርተዋል።

ብዝሃነት ብቻውን የግጭት ምንጭ፣ አንድ ዓይነትነት ብቻውን ደግሞ የሰላም ምንጭ አለመሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዝሃነትን በውስጡ አቅፎ በሰላም የሚኖረው የደቡብ ኦሞ ሕዝብ ለዚህ አብነት ነው ብለዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ትኩረቱን በአርብቶ አደሮች ላይ አድርጎ ሊሰራ የተቋቋመው ፋውንዴሽናቸው በደቡብ ኦሞ ዞን የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን እንደሚያከናውን ገልፀዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ ጋር የሠላም ሚንስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጂንካ ከተማ ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በስታዲየም ያደረጉትን ንግግር አጠናቀው ከአካባቢው የተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም