በኢትዮጵያ ታሪክ ሰርተው ያለፉ ሴቶችን የሚመለከት ጥናት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ታሪክ ሰርተው ያለፉ ሴቶችን የሚመለከት ጥናት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ የካቲት 29/2012 በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ ትላልቅ ተግባራትን የፈፀሙ ሴቶችን ታሪክ ለመሰነድ በምሁራን ጥናት እየተደረገ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር፤ ከደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ከጉራጌ ልማት ማህበርና ከጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ጋር በመሆን አለም አቀፉን የሴቶችን ቀን አክብሯል።
በዓሉ የተከበረው ከ150 አመት በፊት ለሴቶች እኩልነት የታገለችውን የቃቄ ውርዶትን በመዘከር በደቡብ ክልል ወልቂጤ ከተማ ነው።
የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ባላት ረዥም ታሪክ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ የጎላ ነው።
ኢትየጵያን ከችግር ያወጡና በሴቶች ላይ ይደርሱ የነበሩ ጭቆናዎችን፤ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመታገል ዋጋ መክፈላቸውንም አውስተዋል።
ለአብነትም ንግስት አህዋ፣ ንግስት እሌኒ፣ ንግስት ዘውዲቱ፣ ንግስት ጣይቱ፣ የቃቄ ውርዶትና ሌሎች ለአገር ታሪክ የሰሩ ሴቶችን ዘርዝረዋል።
እነዚሀ እንስቶች ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ ከተደቀነባት አደጋ ከወንዶች ጋር በመሆን ከችግር ማውጣት እየቻሉ መሆናቸውን ታሪክ ያወሳል።
የሴቶች እኩልነትን ለማምጣት በመታገል በኩልም አለም ለሴቶች እኩልነት መታገል ከጀመረበት በፊት በኢትዮጵያ እንደነበር ገልጸዋል።
በጉራጌ ዞን ከዛሬ 150 አመት በፊት በሴቶች ላይ የሚደርሰው የባህል ተጽእኖና የወንዶች የበላይነትን በመቃወም ከ10 በላይ የመብት ጥያቄዎችን በመያዝ የታገለች የቃቄ ውርዶትን አንስተዋል።
በመሆኑም የሴቶች እኩልነትን ለማምጣት በኢትዮጵያ ሴቶች መታገል የጀመሩት አለም እያከበረ እንዳለው ከ44 አመት በፊት ሳትሆን ከ150 አመት በፊት መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም ነው ያሉት።
ይህን ታሪክ ለትውልድ ለማስተላለፍና አለም እንዲያውቀው ለማድረግ ስራዎች መጀመራቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ በዘንድሮው ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን የቃቄ ውርዶትን መዘከርም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የደረሱ ጭቆና እና በደል እንጂ የሰሩትን ታሪክ በጥናት በመደገፍ ለትውልድ እንዲሁም ለአለም በማስተዋወቅ በኩል ክፍተት መኖሩንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ጊዜ በማህበራዊ፣ በፖለቲካ እንዲሁም ኢኮኖሚ በተሰማሩበት ዘርፍ ታሪክ እየሰሩ ያሉ ሴቶችን ከቀደሙት ታሪክ ሰሪዎች ጋር በማጣቀስ እንደምሳሌ ለትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ መሆኑንም አብራርተዋል።
"አለም ይህንን ታሪክ እንዲያውቀው እኛ ራሳችን በዛ ታሪክ ውስጥ መኖር መቻል አለብንም" ነው ያሉት።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ከችግር ለማውጣት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ዘርፎች ታሪክ የሰሩ ታላላቅ ሴቶችን ለትውልድ ለማስተዋወቅ የሴቶች ታሪክ በምህራን እየተጠና መሆኑን ሚንስትሯ ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ወደ መጽሃፍ ተቀይሮ ተምሳሌትነታቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ በሰነድ መልኩ እንደሚተላለፍ ነው የገለጹተ።
ታሪክ የሰሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለአሁኑ ትውልድ አርአያ አንዲሆኑና ታሪካቸውን ለአለም ለማስተዋወቅ በኪነጥበብና ሌሎች ተግባራት ይወሳሉ ብለዋል።
ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ለቃቄ ውርዶት መታሰቢያ የወልቂጤ ከተማ ነጋዴ ሴቶች ማህበር በ31 ሚሊየን ብር ለሚያስገነባው ባለ 8 ወለል ህንጻ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
በመርሃ ግብሩ የቃቄ ውርዶትን የተመለከተ ጥናታዊ ጹህፍ፤ የፓናል ውይይትና ሌሎች መርሃ ግብሮች የተከናወኑ ሲሆን መነገው እለትም የትውልድ ስፍራዋ ይጎበኛል ተብሏል።
አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሴቶች ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እኩልነት መስፈን የታገሉትን ለማሰብ የሚከበር ነው።