ቀጥታ፡

የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንሰራለን አሉ

ጋምቤላ (ኢዜአ) የካቲት 29 ቀን 2012 ዓም  የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች የአመለካከት ልዩነቶችን በማስወገድ ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንደሚሰሩ ገለፁ ።

''እኛ ወጣቶች ሰላምን አጥብቀን እንሻለን'' በሚል መሪ ቃል የከተማው ወጣቶች በማርሽ ባንድ የታገዘ የሰላም የእግር ጉዞ ዛሬ አካሄደዋል።

በሰላም የእግር ጉዞው የተሳተፉ ወጣቶች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ብሄርተኝነትና አካባቢዊ አስተሳቦችን በማስወገድ ለከተማው ብሎም ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ወጣት ኦፒዮ ኡቡያ እንደገለፀው የከልሉን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ከመንግስት ጎን እንሰለፋለን ብሏል ።

አካባቢያዊ አስተሳሰቦችና የአመለካከት ልዩነቶች ግጭትን ከመፍጠር ባለፉ ሌላ ጠቀሜታ እንደሌላቸው ነው ወጣቱ የጠቆመው።

ስለሆነም አንድነታቸውንና አብሮነታቸውን በማጠናከር ለክልሉ ሰላምና ልማት እንደሚሰሩ ወጣት ኦፒዮ ተናግሯል ።

ሰላም ለሰው ልጆች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መሰረት መሆኑን የገለጸው ደግሞ ሌላው ተሳታፊ ወጣት ናስር ሯች ነው።

በመሆኑም ሰላም በሌለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች እያጋጠሟቸው ያሉትን ፈተናዎችና ችግሮች በመገንዘብ ለአካቢያቸው ዘላቂ ሰላም ተግተው እንደሚሰሩ ገልፇል ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የክልሉ ሰላማና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶማስ ቱት በፕሮግራሙ ላይ እንደተናገሩት በክልሉ የተገኘውን ሰላም ቀጣይነት ለማረጋግጥ በሚደረገው ጥረት ከወጣቱ የላቀ ሚና ይጠበቃል ብለዋል።

ቀደም ሲል በክልሉ የተለየዩ ግጭቶች ሲከሰቱ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ ሰላም መኖሩን ተናግረዋል።

በመሆኑም በክልሉ ያለውን ሰላም ቀጣይነት በማረጋገጥ የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ወደ ፊት ለማራመድ  ከወጣቱ ኃይል ብዙ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል ።

በዕለቱ በክልሉ ያለውን ሰላም ይበልጥ ለማጠናክር ወጣቶቱ ላካሄዱት የሰላም የእግር ጉዞ ለአዘጋጀው የጋምቤላ ሰላምና ልማት ግንባታ ማዕከል ምስጋናቸው አቅርበዋል ።

የጋምቤላ የሰላም ማዕከል ዋና ዳሬከተር አቶ አይተን አንማው እንዳሉት ደግሞ በክልሉ በህዝቦች መካከል የሰላም ችግሮች እንዳይከሰቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ማዕከሉ በቀጣይም ጅምር ስራዎቹን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የሰላም የእግር ጉዞው በሀገር መከላከያ የማርሽ ባንድ በመታጀብ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ተከናውኗል ።         

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም