ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ሰኔ22/2010 ዘጠኝ ቡድኖች የሚሳተፉበት የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ከጠዋቱ 3 ሰአት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከከምባታ ዱራሜ ይጫወታሉ። በክልል ከተማ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከመከላከያ ከጠዋቱ 3 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ከነገ በስቲያ ደግሞ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ጠዋት ፌዴራል ማረሚያ ከፌደራል ፖሊስ እንዲሁም መቐለ ከተማ በሜዳው ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በተመሳሳይ ከጠዋቱ 3 ሰአት ላይ የሚጫወቱ ይሆናል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ24 ነጥብ ሲመራ፣ መቐለ ከተማ በ19 ነጥብ ሁለተኛ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማና ፌዴራል ፖሊስ በተመሳሳይ 18 ነጥብ እርስ በርስ ሲገናኙ ያሸነፈ በሚለው ህግ በቅደም ተከተል ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል። ቡታጅራ ከተማ 2 ነጥብ ብቻ ይዞ በዘጠነኛ ደረጃ ላይ የሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጧል። ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሶስት ሳምንት የጨዋታ መርሃ ግብሮች የሚቀሩት ሲሆን  መርሃ ግብሩን ለማስተካከል የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ ለውጥ ሊደረግ እንደሚችል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም