የኢትዮጵያን የአባይ ውሃ የተጠቃሚነትን መብት ከዳር ለማድረስ እንታገላለን... ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የአባይ ውሃ የተጠቃሚነትን መብት ከዳር ለማድረስ እንታገላለን... ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን የአባይ ውሃ የተፈጥሮ ተጠቃሚነት መብት ከዳር ለማድረስ በጽናት እንታገላለን አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን።
"እውነትን ይዘን በጥበብና በዲፕሎማሲ ክብር እና መብታችንን ለማስከበር እንራመዳለን፤ በሁሉም መንገዶችም እናሸንፋለን" ብለዋል አቶ ደመቀ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቃለ-ምልልስ አካሂደዋል።
በዚህ ወቅት እንዳሉት "የተፈጥሮ ሃብት የመጠቀም መብታችን የማይገሰስ ፤ ለዘመናት የዘገየ ነገር ግን የግድ መሆን ያለበት ነው"።
ይህ ሲሆን ግን ምክንያታዊ በሆነና የሁሉንም ተጠቃሚነት ባረጋገጠ ፤ የታችኛው ተፋሰስ አገራትንም በማይጎዳ መልኩ ሊሆን ይገባል ይላሉ።
በኢትዮጵያም ይህ በሚገባ ታስቦበት እየተሰራበት ያለ በመሆኑ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት "እውነትን የሚያዳምጥና ለእውነት የቆመ እስካለ ድረስ እጅግ ተገቢነት ያለው ነው" ብለዋል።
ግብጽ ከመሰረቱ የግድቡን እውን መሆን የማትፈልግ ቢሆንም በተለይ በአሁኑ ወቅት የውሃ የመሙያ ጊዜው ሲደርስ ለተለያዩ አካላት ተበዳይ መስላ በመቅረብ ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ እየሰራችና የተለያዩ ዘመቻዎች እያካሄደች ትገኛለች።
"ይሁንና ለዘመናት የኖረው፤ በዚህ ዘመን ደግሞ ይህ ትውልድ ወደፊት በመምጣት ሌላ ሃብት ባይገኝ እንኳን በራሴ እሰራዋለሁ ብሎ ደፍሮ እዚህ ያደረሰውን ፕሮጀክት ወደኋላ መመለስ አይቻልም" ብለዋል።
በዚህ ዘመን አገሮች የየራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም የመወዳደርና የመጠቀም መብት ላይ ሲሰሩ ይታያል።
ኢትዮጵያም የራሷን ጥቅምና መብት ለማስከበር የማንንም ፈቃድ እንደማትጠይቅ፤ ይሁንና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ነገሮች ተጠንተው ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በግልጽ በሚደረግ ውይይት ሁሉንም የሚጠቅም ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል እምነቷ መሆኑን አሳውቃለች።