ቀጥታ፡

የደቡብ ኦሞ አርብቶ አደሮችን አኗኗር ለመለወጥ በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ የሚመራ የጥናት ቡድን ተቋቋመ

አዲስ አባበ፤የካቲት 29/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ኦሞ ዞን የሚኖሩ አርብቶ አደሮችን አኗኗር ለመለወጥ የሚያስችሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመለየት በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ የሚመራ ቡድን ጥናት ያደርጋል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ በመገኘት ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል።

የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የግብርና ልማትን ማዘመን፣ የውኃ እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ማሻሻል በውይይቱ ወቅት ከተነሱት ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በምላሻቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የመንግሥትን አቅም ከግምት ውስጥ ማስገባት ይጠይቃል ብለዋል።

በክልል አደረጃጀት ዙሪያ ለተነሳላቸው ጥያቄም መዋቅር በሰፋ ቁጥር ተጨማሪ በጀት ስለሚጠይቅና በጀትም የማይኖር በመሆኑ ጥቅምና ጉዳቱን መለየት ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህም በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራ የጥናት ቡድን በአካባቢው የሚኖሩ አርብቶ አደሮችን አኗኗር ለመለወጥ የሚያስችሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመለየት ጥናት ያካሂዳል ተብሏል።

ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ ጋር የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የሠላም ሚንስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጂንካ ከተማ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም