ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በመላው ዓለም በመከበር ላይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በመላው ዓለም በመከበር ላይ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29/2012 (ኢዜአ) የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) በተለያዩ ዝግጅቶች በመላው ዓለም በመከበር ላይ መሆኑን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል።
በተባበሩት መንግስታት የሴቶች ጉዳይ ዋና ዳይሬክተር ፑምዚል መላምቦ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን (ማርች 8) በማስመልከት መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ከመከበር ባለፈ በስርአተ ፆታ እኩልነት ዙሪያ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ የሚሰራበት አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።
“ዓለም ለሁሉም ፍትሃዊ መሆን አለባት፤ በሰው ልጆች እኩልነት ላይ ፊትና ኋላ የሚባል ነገር መኖር የለበትም” ሲሉም ተናግረዋል።
"ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ዛሬ ስናከብረው በርካታ መሻሻሎች በታዩበት አጋጣሚ ቢሆንም አሁንም የሚቀሩን የቤት ስራዎች አሉ" ያሉት ዳይሬክተሯ በተለይ በትምህርት ተሳትፎ፣ በስራ ጫና፣ በመብት ጥሰትና ሌሎችም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ወንጀሎች ቀጣይ የቤት ስራዎቻችን ናቸው ብለዋል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከሆነ በአሁኑ በቅት በዓለም ላይ ከ10 ሴቶች መካከል አንዷ መፃፍና ማንበብ አትችልም።
ይህ ደግሞ ሴቶች በቤት ውስጥ ስራና በቤተሰብ ሃላፊነት ጫና ተጠምደው የመማር እድል ባለማግኘታቸው የተፈጠረ ክፍተት መሆኑን አስረድተዋል።
ያም ሆኖ በዓለም ላይ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተስፋ የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።
በዓለም ላይ 131 አገሮች የስርአተ ፆታ እኩልነትን እውን ለማድርግ የህግ ማሻሻያ ማድረጋቸው ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆኑንም አብራርተዋል።
በሴቶች ላይ የሚደርስን የቤት ውስጥ ጥቃት ለመከላከል በተለያዩ አገሮች የሚታዩት የመፍትሄ እርምጃዎችም ተስፋ የሚሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የሴቶችን የእኩልትና የፍትሃዊነት ችግሮች ለመፍታት እንቅስቃሴ የተጀመረበት እለት ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ይከበራል።
የዘንድሮው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ109ኛ ጊዜ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ44ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።