የደቡብ ኦሞ ህዝብ የህብረ ብሄራዊና የመደመር መገለጫ ነው- ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ኦሞ ህዝብ የህብረ ብሄራዊና የመደመር መገለጫ ነው- ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29/2012 ዓ. ምጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የደቡብ ኦሞ ህዝብ የህብረ ብሄራዊና የመደመር መገለጫ ተምሳሌት መሆኑን ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ በስታዲየም ለተሰበሰቡት የአካባቢው ህዝብ ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም ደቡብ ኦሞን "ትንሿ ኢትዮጵያ፣ የህብርና የአብሮነት መገለጫ እንዲሁም በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ታላቅ ህዝብ" የሚኖርበት ሲሉ አወድሰዋል።
የኦሞ ሸለቆም ልክ እንደ አፋር ሁሉ በሰው ልጆች የአኗኗር ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑን አንስተዋል።
አካባቢው ታሪካዊና በብዙ ጎብኝዎች የሚዘወተር እንዲሁም የኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊነት አንዱ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።
የደቡብ ኦሞ ህዝብ መደመርን ቀድሞ የተረዳ ከሰው ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋርም የተለያዩ እሴቶችን አካብቶና አሰባስቦ የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
የደቡብ ኦሞ የእርቅና የባህላዊ ዳኝነት ስርአትም ሰፊ ትምህርትና ተሞክሮ የሚቀሰምበት ድንቅ ባህላዊ እሴት መሆኑን አብራርተዋል።
ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ ጋር የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ የሠላም ሚንስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጂንካ ከተማ ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በስታዲየም ያደረጉትን ንግግር አጠናቀው ከአካባቢው የተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ናቸው።