የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ሰኔ 22/2010 የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። በተስተካካይ ጨዋታዎችና በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የጥሎ ማለፍ ውድድር ምክንያት ለሁለት ሳምንት ሳይካሄዱ የቆዩት የሊጉ መደበኛ መርሃ ግብሮች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የሚጀምር ይሆናል። በዚሁ መሰረት ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰአት መከላከያ መውረዱን ካረጋገጠው ወልዲያ ከተማ ጋር ይጫወታል። ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰአት ኢትዮ ኤሌትሪክ ከፋሲል ከተማ፣ ከቀኑ 11 ከ30 ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በክልል ከተሞች በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ጅማ አባጅፋር ከደደቢት፣ በአዲግራት ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከአዳማ ከተማ፣ አርባምንጭ ከተማ በሜዳው ከሃዋሳ ከተማ እንዲሁም በይርጋለም ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከመቐለ ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ የሚጫወቱ ይሆናል። ሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ይጫወታሉ። የሶስት ሳምንታት መርሃ ግብር በቀረው የዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ለመሆንና ከሊጉ ላለመውረድ የሚደረገው ፍልሚያ አጓጊ ሆኗል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ጅማ አባጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 48 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናና መቐለ ከተማ በተመሳሳይ 46 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከትል ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ኢትዮ ኤሌትሪክ፣ አርባምንጭ ከተማና መውረዱን ያረጋገጠው ወልዲያ ከተማ በቅደም ተከተል ከ14 እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የጅማ አባጅፋር ተጫዋች ናይጄሪያዊው ኦኪኪ አፎላቢ በ17 ግቦች ሲመራ፣ ናይጄሪያዊው የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ሳሙኤል ሳኑሚ በ13 የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ በ12 ግቦች ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ይከተላሉ።