የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡበት መሆኑን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡበት መሆኑን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ገለጹ
አዲስ አበባ የካቲት 29/2012 ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ሴቶች በተለያዩ መስኮች የሚያደርጉት ተሳትፎ የሚበረታታና ቀጣይ ውጤቶችም የሚመዘገቡበት መሆኑን ገለጹ።
ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አስመልክቶ በሴቶች ብቻ የሚመራ የበረራ ቡድን ትላንት ማምሻውን ወደ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ አቅንቷል።
ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የሴቶች ጉዳይ በዓመት አንድ ቀን ብቻ ታስቦ የሚቀር ሳይሆን በየቀኑ ሊሰራበት የሚገባ ነው ።
በአገሪቷ አሁን እየታዩ ያሉ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚበረታታና ወደ ፊትም በርካታ ውጤቶች ሊመዘገቡበት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የተያያዘችውን የለውጥ ጎዳና ለማሳደግ ሴቶችን በተለያዩ መስኮች ተሳታፊ ማድረግ እንዲሁም በትምህርት ማብቃት ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በርካታ ሴቶች ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም የሴቶች ጉዳይ ለሴቶች ብቻ የሚተው ባለመሆኑ በማሕበራዊ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ መስክ ተሳትፏቸውን ለማጠናከር የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በበኩላቸው አየር መንገዱ ሴቶችን በማብቃት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ መሆኑን አንስተዋል።
በተቋሙ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ 32 በመቶ በሃላፊነት ቦታ ላይ የሚሰሩት ሴቶች መሆናቸውን ገልጸው ሴቶች የተለየ እገዛ የሚፈልጉ ሳይሆን የተሰጣቸውን ሃላፊነት የሚወጡ ለመሆናቸው በርካታ ማሳያዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሴቶችን ቀን አስመልከቶ በየዓመቱ በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ ያደርጋል፤ የዘንድሮውም ለ6ኛ ጊዜ ነው።