ቀጥታ፡

ከአገር ሊወጡ የነበሩ ከ3 ሺህ በላይ ወጣቶች ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ተደረገ

ደሴ ኢዜአ የካቲት 29 /2012 በደቡብ ወሎ ዞን የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በተሰራው ቅንጅታዊ ስራ ከአገር ሊወጡ የነበሩ ከ3 ሺህ በላይ ወጣቶች ተይዘው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መደረጉን የዞኑ ሰራተኛና ማህራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።

የደቡብ ወሎ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሉባባ አብዱ ለኢዜአ እንደገለፁት አካባቢው በህግ ወጥ ደላሎች ተታለው ወደ አረብ ሃገራት የሚጓዙ ወጣቶች መሸጋገሪያ እየሆነ መጥቷል ።

የችግሩን አስከፊነት በመረዳት የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር ህገ ወጥ ተጓዥችንም ሆነ ደላላዎችን የመያዝ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል ።

ባለፉት ጥቂት ወራት በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጡ ሲሉ ተይዘው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ከተደረጉት 3 ሺህ ወጣቶች መካከል አብዛኛዎቹ በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው ።

ወጣቶቹ ከአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በህገ ወጥ ደላሎች ተታለው ለስደት የተነሳሱ እንደነበሩ ከመምሪያ ኃላፊዋ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሒደት  ዋነኛ ተሳታፊ የነበሩ ከ25 በላይ ህገ ወጥ ደላሎችም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቃሉ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል የሥራ ሂደት ባለቤት ኮማንደር ይመር አባተ በበኩላቸው በህገ ወጥ መንገድ በደጋን ባቲ በኩል ለመውጣት ሲሞክሩ የነበሩ 3 ወጣቶች ህይወታቸው አልፏል ።

ሌሊት ጭምር ጫካ ለጫካ በእግራቸው ረጅም ርቀት ተሹለክልከው ለመውጣት ይሞክራሉ ያሉት ኮማንደር ይመር ከ10 ዓመት በታች ያሉ ህጻናት ሳይቀሩ በተሳሳተ መረጃ ከቤተሰቦቻቸው እየተለዩ ለችግር እየተዳረጉ ነው ብለዋል ።

ህገ ወጥ ደላሎቹ ከወጣቶቹ እስክ 300 ሺህ ብር ድረስ ከአገር የማውጫ ገንዘብ እንደሚጠይቁም ኮማንደሩ ተናግረዋል ።

ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ በዘመናዊ መሳሪያና ተሸከርካሪ ጭምር የታጀቡ መሆናቸውን ገልፀው ችግሩን ለመከላከል ህብረተሰቡ ከፀጥታ መዋቅሩ ጎን ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ በበኩላቸው የችግሩን አሳሳቢነት መንግስት ተገንዝቦ ከፌደራል እስከ ወረዳ ድረስ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በመስራቱ ለውጦች እየታዮ መሆኑን ተናግረዋል ።

በችግሩ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጥቂት አመራሮችና የጸጥታ ኃይሎች ጭምር መኖራቸው ችግሩን ውስብስብ እንዳደረገው ዋና አስተዳዳሪው ገልፀው ከአጎራባች ክልሎች፣ ዞኖችና ህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተን ለመከላከል በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል ፡፡

በቃሉ ወረዳ የሀርቡ ከተማ ነዋሪ ወጣት ከድር አለሙ በዚህ ዓመት መጀመሪያ በባቲ በኩል ወደ አረብ አገር በህገ ወጥ መንገድ ለመውጣት ሲሞክር በፖሊስ ተይዞ ወደ ቤተሰቦቹ እንዲመለስ መደረጉን ተናግሯል ።

እስከተያዘበት እለት ስቃይና መከራን አስተናግጃለሁ ያለው ወጣቱ በደላሎች ተታለው ሌሊት ሰሌዳ ቁጥር  በሌለው መኪና እየተጫኑ የተወሰኑ አካባቢዎችን አልፈው እንደነበረም ገልጿል፡፡

ሃያ አንድ ሆነው ጨካ ለጫካ እግራቸውን እስኪላጥ ድረስ ቢጓዙም አፋር ክልል ላይ በፖሊሶች ተይዘው መመለሳቸውን አስረድቷል ።

ሌላዋ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ እመቤት ደምሰው በበኩላቸው የ9ኛ ክፍል ወንድ ልጃቸው ትምህርት ቤት በሄደበት ደላሎች በ500 ብር አታለው በህገ ወጥ መንገድ ጉዞ እንዳስጀመሩት አስታውሰዋል፡፡

ጉዳዩን ስሰማ አቅሌን ብስትም ልጄን ማግኘት ባለመቻሌ ከመጸለይ ውጭ መፍትሄ አላገኘሁም ነበር ብለዋል፡፡

በአንድ ወቅት ስልክ ደውሎ የመን ደርሻለሁ እንዳላቸው አስታውሰው ለ4 ወር ያህል ድምጹ በመጥፋቱ ሞቷል ብዬ ተስፋ ቆርጬ ነበር የሚሉት ወይዘሮዋ ከእርሱ ጋር ከሄዱት መካከል የሞቱ እንዳሉ መርዶ መነገሩን ገልፀዋል ።

 በጭንቀትና ውጥረት ውስጥ እያሉ  የወንድሞቻቸው ልጆች ከ200 ሺህ ብር በላይ ከፍለው የመን ከታገተበት አስለቅቀው ሳውዲ አንዳስገቡት ሲነግሩኝ ደግሞ ተደስቼ ነበር ብለዋል፡፡

ነገር ግን እዳውን እንኳን ሳይከፍል ተይዞ መምጣቱንና ትምህርቱንም አቋርጦ እኔንም ባለ እዳ አደርጎኛል ያሉት ወይዘሮ እመቤት ወጣቱ በአገሩ ሰርቶ የመለወጥ ባህሉን እንዲያጎለብት መክረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም