ኦነግ ሸኔ በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ለመከላከል ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል - የኦሮሚያ ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
ኦነግ ሸኔ በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ለመከላከል ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል - የኦሮሚያ ፖሊስ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች ኦነግ ሸኔ በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ለመከላከል የክልሉ ፖሊስ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚያጠናክር አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል ምርመራ ዘርፍ የፍትህ ማሰጠት ሃላፊ ግርማ ጋላን ጉዳዩን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ የክልሉ ፖሊስ አገራዊ ለውጡ እንዳይደናቀፍ ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ ሲወስድ ቆይቷል።
ያም ሆኖ በንፁሃን ዜጎች፣ በአገራዊ ለውጡና በመጪው የምርጫ ሂደት ላይ ስጋት ተደቅኗል።
መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየሰራ ያለው ስራ እንዳይስተጓጎልና አገራዊ ለውጡ እንዳይደናቀፍ እርምጃ እየተወሰደ ቢሆንም ትንኮሳው በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን አስታውቀዋል።
ኦነግ ሸኔ በየጊዜው በሚፈጽመው ጥቃት በንጹሃን ዜጎችና በፖሊስ አባላት ጭምር የሞትና የአካል ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በጸጥታ ስጋት ምክንያት በአካባቢው በመንግስትም ሆነ በግል የሚሰሩ መሰረተ ልማቶች መቆማቸውንም ጠቁመዋል።
ኦነግ ሸኔ በሠላማዊ ትግል በምርጫው እንሳተፋለን ከሚሉ ሃይሎች ጋር በረቀቀ መንገድ በመመሳጠር አካባቢውን የማተራመስ ዕቅድ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑ ፖሊስ መረጃ አለው ነው ያሉት።
ይህ ሃይል ራሱ ችግር እየፈጠረ በሌላ በኩል ፖሊስ ያልተገባ እርምጃ እየወሰደብኝ ነው በማለት በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች እየከሰሰ ነውም ብለዋል።
ከተለያዩ አካላት በሚያገኘው የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ በአገሪቱ ሊካሄድ የታሰበውን አገራዊ ምርጫ ለማስተጓጎል እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ ከዚህ በኋላ የክልሉ ፖሊስ ኦነግ ሸኔ ከዚህ ድርጊቱ የማይቆጠብ ከሆነ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በትዕግስት እንደማይመለከትና የማያዳግም እርምጃም እንደሚወስድ አስታውቀዋል።
ይህንን ቡድን በገንዘብም ይሁን በቁሳቁስ የሚደግፉ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
አያይዘውም የክልሉ ፖሊስ ከአጎራባች ክልሎች ጋር የአካባቢውን ሠላም ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።