ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ የመጠቀም መብቷ አለም አቀፉን መርህ የተከተለ መሆኑን ምሁራን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ የመጠቀም መብቷ አለም አቀፉን መርህ የተከተለ መሆኑን ምሁራን ገለጹ
አርባምንጭ፣ የካቲት 28/2012( ኢዜአ ) ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ የመጠቀም መብቷ አለም አቀፍ መርህን የተከተለ አካሄድ መሆኑን የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን በሰጡት አስተያየት ድንበር አቋርጠው የሚያልፉ ወንዞችን ሀገራት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መጠቀም እንዳለባቸው ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም መርህ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንትፊክ ዳሬክተር ዶክተር አብደላ ከማል እንዳሉት ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚዋ እያደገ በመምጣቱ የአባይን ወንዝ ጥቅም ላይ ማዋሉ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው፡፡
የሀገር ውስጥና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዕድገትን ተከትሎ የሀገሪቱ የኃይል ፍላጎት በየዓመቱ ከ20 እስከ 30 በመቶ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡
"የህዳሰው ግድብ ተፋሰሱ ሀገራትን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው "ያሉት ዶክተር አብደላ በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባው የአስዋን ግድብ የውሃው አቅም ከግድቡ በላይ በሚሆንበት ጊዜ ግድቡን በማስተንፈስ በከፍተኛ ሁኔታ ሲባክን የነበረውን የውሃው መጠን ለመቆጣጠር እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪ በጎርፍና ደለል ምክንያት በየዓመቱ ጉዳት ሲደርስባቸው የነበሩ የሱዳንና ግብጽ ህዝቦች ከስጋት የሚታደግ ይሆናል ብለዋል።
"ውሀው ኃይል ካመነጨ በኋላ ወደ ቀድሞ ፍሰቱ የሚመለስ በመሆኑ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን የሚጎዳ አይደለም "ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የውሃ ሀብት ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ሳሙኤል ደገሌ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከ86 በመቶ በላይ የወንዙ አመንጪ እንደመሆኗ የመጠቀም ዓለም አቀፋዊ መብት እንዳላትም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መሰረት በማድረግ ዓለም አቀፍ መርህን አክብራ እያለች ጫና ለመፍጠር የሚፈልጉ ሀገራት ሚዛናዊና ምክንያታዊ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የዘርፉ ምሁር አቶ አበራ ኤርሚያስ በበኩላቸው የወንዙ ፍሰት ክረምት ላይ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ በዚህን ወቅት ለመሙላት መታቀዱ የታችኞች ተፋሰስ ሀገራት ላይ የውሃው መጠን እንዳይቀነስ ታስቦ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።
"ግድቡ በኢኮኖሚ የቀጠናውን ሀገራት የሚያስተሳስር በመሆኑም የሀገራትን አንድነትና ትብብር ሂደት ከፍ የሚያደርግ ነው" ሲሉም አመላክተዋል፡፡
በዓለም አቀፍ መርህ መሠረት ከአሜሪካ ወደ ሜክሲኮ የሚፈሱ ወንዞችን በፍትሃዊ መንገድ እየተጠቀሙ እንዳሉ ሁሉ ኢትዮጵያም ከተፋሰስ ሀገሮች ጋር ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የአባይን ወንዝ እንጠቀም ማለቷ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።