የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና ከሰኔ 30 ጀምሮ በአዲስ አበባ ይሰጣል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና ከሰኔ 30 ጀምሮ በአዲስ አበባ ይሰጣል
አዲስ አበባ ሰኔ 21/2010 የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና ከሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ይሰጣል። እስከ ሐምሌ 10 በሚቆየው ስልጠና ከክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች የተወጣጡ ከ24 የሚበልጡ አሰልጣኞች እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ስልጠናውን የሚሰጡት በአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአሰልጣኝ መምህርነት ደረጃ ያላቸው ሁለት አሰልጣኞች ሲሆኑ ከኢትዮጵያ አቶ አድማሱ ሳጂ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና ከኬንያ ሚስተር ሳሙኤል ላታባ ናቸው። በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆኑ፣ በአገር ውስጥ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና የወሰዱና በአሁኑ ሰዓት ደግሞ አትሌቶችን በማሰልጠን ላይ የሚገኙ በስልጠና ላይ ተሳታፊ መሆን እንደሚችሉ ፌዴሬሽኑ ገልጿል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወቅቱ ከደረሰበት ሳይንሳዊ የአትሌቲክስ ስልጠና ጋር አብሮ መጓዝ እንዳለበት እንደሚያምን ጠቁሟል። በዚህም መሰረት በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ክልሎችን፣ ከተማ አስተዳደሮችን፣ የአትሌቲክስ ስልጠና ፕሮጀክቶችን፣ ማሰልጠኛ ማእከላትንና ልዩ ተቋማትን በዘመናዊ ስልጠና በማገዝ አቅማቸውን ማሳደግ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቀዳሚ አጀንዳ እንደሆነም አመልክቷል። የሚሰጠው የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአንደኛ ደረጃ ስልጠና የአለም የአትሌቲክስ ሳይንሳዊ ስልጠናን ከመከተል አንጻር የተዘጋጀ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።