የአሰላ ከተማ አስተዳደር የህብረሰተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚያግዝ ግንባታ እያካሄደ ነው

አዳማ ፣የካቲት 28/2012 ( ኢዜአ) የአሰላ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚያግዝ የመሰረተ ልማት ግንባታ እያካሄደ መሆኑን ገለጸ።

የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገብሬ ዑርጌሶ ለኢዜአ እንዳሉት ከስራዎቹ መካከል ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ የድንጋይ ንጣፍ፣ ጠጠር አስፓልት መንገድ  ግንባታ ፣ የነባር ጥገና፣ የፍሳሽና ጎርፍ ማውረጃ ቦዮች ይገኙበታል።

የመጠጥ ውሃ ማሻሻያ ፣የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የማምረቻና መሸጫ ማዕከላት ሌሎች እየተሰሩ ያሉ  ልማቶች ናቸው።

"አስተዳደሩ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በሙሉ አቅሙ እየሰራ ነው " ያሉት ከንቲባው በተለይ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ የበጀት ዓመቱ ቁልፍ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።

ለልማት ስራዎቹ ማስፈጸሚያ  ከፍተኛ በጀት ከመመደብ ባሻገር ህብረተሰቡ በጉልበቱ፣ በገንዘቡና በዕውቀቱ  እያገዘ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት በተጨማሪ በግንባታ ላይ የሚገኙ አብዛኞች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከ60 በመቶ በላይ መከናወናቸውን አስረድተዋል።

ግንባታዎቹ እስከ መጪው ሰኔ ወር ድረስ ሁሉም ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ ከ150ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ከንቲባው ተናግረዋል።

ከአሰላ ከተማ ቀበሌ 14 ነዋሪዎች መካከል  ወይዘሮ  አልማዝ ፀጋዬ በሰጡት አስተያየት በክረምት ወቅት  መኖሪያ ቤታቸው በጎርፍ እየተጥለቀለቀ ለጉዳት እንደሚጋለጡ ተናገረዋል።

በአሁኑ ወቅት አስተዳደሩ ችግራቸውን ለመፍታት  የፍሳሽና ጎርፍ መውረጃ ቦዮችን ክረምት ሳይገባ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በገንዘብና  በጉልባት ከአስተዳደሩን ጎን በመሆን ባበረከቱት አስተዋጽኦ  ሽልማትና የምስጋና ምስክር ወረቀት ከተሰጣቸው ሰዎች መካከል አንዷ መሆቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ አልማዝ ለልማት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉበትም ተናግረዋል።

በከተማዋ የቡርቂቱ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብዱልቡሃሪ አብደላ በበኩላቸው ከ17 ዓመት በላይ ረጅም አገልግሎት የሰጡ መንገዶቹ ጥገና ሳያገኙ የህዝብ የቅሬታ ምንጭ ሆነው መቆየታቸውን  ተናግረዋል።

የከተማ  አስተዳደሩ ዘንድሮ እየሰራ ያለው ልማት የሚበረታታ  መሆኑን ገልጸዋል።

የልማት ስራው ከዳር  እንዲደርስ የበኩላቸውን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው "እየተከናወነ ያለው  መሰረተ ልማት ተጠናቆ ለአገለግሎት እንዲበቃ እገዛችንን አጠናክረን እንቀጥላለን "ብለዋል።

በተለይ የአሰላ ከተማ አቀማመጥ መሬቱ ታዳፋት በመሆኑ የጎርፍ ተጋላጭ እንደሆኑ ጠቁመው የፍሳሽና የጎርፍ መውረጃ ቦዮች መሰራታቸው ከስጋት እንደሚያላቅቃቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም