ኢትዮጵያ የህዳሴን ግደብ ለመገንባት የማንም ፈቃድ እንደማያስፈልጋት ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የህዳሴን ግደብ ለመገንባት የማንም ፈቃድ እንደማያስፈልጋት ተገለጸ
አክሱም፣ የካቲት 28/2012( ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የህዳሴ ግድብን ገንብታ ተጠቅማ ለመሆን የማንንም ፈቃድ መጠየቅ እንደማያስፈልጋት በአክሱም ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።
ከነዋሪዎቹ መካከል በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ወልደስላሴ ወልደሚካኤል "ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷ የሆነውን በአባይ ወንዝ የመጠቀም ሙሉ መብት መብት አላት" ብለዋል።
ሀገሪቱ አሁን የያዘችው አቋምም ተገቢ እንደሆነ ጠቅሰው ግድቡን የመገንባትና የመጠቅም መብቷ በጎረቤት ሀገራት መሪዎች ሳይቀር እውቅና እንዳላት ገልጸዋል።
''አብረን እንገንባ አብረን እንጠቀም'' የሚል የኢትዮጵያ መርህ በአለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
"የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከድህነት የምንወጣበት ዋነኛ ጉዳይ በመሆኑ መንግስት የሀገርንና የህዝብ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ማስቀጠል አለበት" ብለዋል።
መንግስት ተቀዛቅዞ የነበረውን የህዝቡ የሞራል፣ የገንዘብ እና ሃሳብ ድጋፍ ማስቀጠል እና ሀገራዊ ወኔ ማጠናከርም እንዲሁ።
በዩኒቨርሲቲው የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ዳንኤል አዲስ በበኩሉ በግድቡ ዙሪያ ያሉ ጣልቃ ገብነቶች ተቀባይነት እንደሌለው መንግስት በማስታወቅ የያዘው አቋም የሚደገፍ መሆኑን ተናግሯል።
በአክሱም ከተማ የሐወልቲ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሰላም መኮንን በሰጡት አስተያየት በግድቡ ጉዳይ ጣልቃ የገቡ አካላት እንዳሉ በመገናኛ ብዙሃን መስማታቸውን ገልጸዋል።
መንግስት የያዘውን አቋም እንደሚደግፉትም ተናግረዋል።
"ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የሀገር ጉዳይ ነው፣ የሀገር ጉዳይ ለድርድር መቅረብ የለበትም፤ የራሳችን በራሳችን የመወሰን መብት አለን" ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያስተሳሰረ፣ የባለቤትነት መንፈስን ያጠናከረ እና የብሄራዊ አንድነት መገለጫ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ግድቡን በመገንባት የተፈጥሮ ሃብቷ የማልማትና መጠቀም መብቷ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ የማንም ፍቃድ መጠየቅ እንደማያስፈልጋት አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።