ቀጥታ፡

አመራሩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በአግባቡ መምራት ይጠበቅበታል

ባህርዳር፣ የካቲት 28/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል አመራሩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በአግባቡ በመምራት የብልጽግና ጉዞን ለማፋጠን በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅበት ተገለጸ።

የክልሉ ብልጽግና ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና መጠናቀቅን ተከትሎ ፓርቲው የሚመራው  የክልሉ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር የመሰረተ ልማት አማካሪ አቶ ደሳለኝ አስራደ  ለኢዜአ እንደገለጹት  ከለውጡ በፊት  የመሰረተ ልማት ስርጭት ፍትሃዊነት የጎደለው ነበር።

በአማራ ክልል ከሚገኙት26 የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ሳብስቴሽኖች የተሻለ አቅም ያላቸው ሰባቱ ብቻ ናቸው።

ቀሪዎች ከአገልግሎት ብዛት አንጻር ያረጁና መለዋወጫ የማይገኝላቸው እንዲሁም ከደረጃ በታች መሆናቸውን አቶ ደሳላኝ ጠቅሰዋል።

በቴሌ ኮሙዩኒኬሽንና በመስኖ ግንበታ የተሻለ ቢሆንም በመንገድ ግንባታ ዘግይቶ መጀመር፣ መጓተትና፣ ከደረጃ በታች መሆን ህዝቡን ወደ ቅሬታ አስገብቷል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የክልሉ መንግስት ከፌደራል ተቋማት ጋር በቅርበት በመስራት የነበሩ ችግሮች መታረማቸውን ጠቅሰው ይህም የመሰረተ ልማት ሃብት አመዳደብን በማስተካከል ለውጥ እንዲመጣ  ማስቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና አዳዲስ በማስጀመር የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ጥረት በመደረጉ  ባለሃብቶችና ድርጅቶችን መሳብ ተችሏል ብለዋል።

ሆኖም በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸም ስርቆትና ዝርፊያን አለመቆጣጠርና ራሱን የቻለ እቅድ አዘጋጅቶ ህብረተሰቡን በማስተባበር አለመምራት የተከሰቱ ችግሮች ናቸው።

አሁን ላይ ሰልጥኖ የወጣው  አመራርም የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በአግባቡ በመምራት የክልሉን ህዝብ ወደ ብልጽግና ጉዞ እንዲገስገስ በኃላፊነት መስራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

 ከባህርዳር የስልጠናው ተሳታፊ አቶ ሸጋው ፈንቴ እንዳሉት ስልጠናው እስካሁን የተበታተነውን ኃይል ወደ አንድ በማምጣት በልማት የበደለውን ህዝብ ለመካስ የሚያግዝ ነው።

በተለይም የመሰረተ ልማት ዘርፉን በማሳደግ ክልሉን በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተወዳዳሪ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ተናግረዋል።

ለዚህም አመራሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በማስፈጸም ረገድ መተጋገዝንና  መተባበርን በማቀናጀት  የብልጽግናን ጉዞ ለማሳከት የሚረባረብበት እድል መመቻቸቱን ገልጸዋል።

 ከምስራቅ ጎጃም የስልጠናው ተሳታፊ አቶ አብዮት ጎኔ በበኩላቸው ስልጠናው  ቀደም ሲል የተፈጠሩ ስህተቶችን በማረም በቀጣይ ሀገርና ህዝብን ለመጥቀም የሚያስችል እውቀትና ክህሎት ያስጨበጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።

"በብልጽግና ማንኛውም የልማትና የፖለቲካ አፈጻጸም እውነትን፣ ተጨባጭነትንና ሳይንስን መሰረት ያደረገና  በተግባር እየተረጋገጠ የሚሄድ መሆን እንዳለበት ያስገነዘበን ነው"ብለዋል።

ይህም ሰው በሰውነቱ ብቻ የሚከበርበት ስርዓት ለመገንባት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ማመቻቸቱን አመልከተዋል።

በክልሉ ስድስት ማዕከላት ሲካሄድ በቆየው ስልጠና ከ10ሺህ በላይ የብልጽግና  ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች መሳተፋቸውን ቀደም ብሎ ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም