ቀጥታ፡

ፋኦ ለአንበጣ መከላከል ድጋፍ እንዲውሉ ከተከራያቸው 3 አውሮፕላኖች አንዱን አስረከበ

አዲስ አበባ የካቲት 27/2012 (ኢዜአ) የአለም የእርሻና ምግብ ድርጅት (ፋኦ) ለአንበጣ መከላከል ድጋፍ እንዲውሉ ከተከራያቸው ሶስት አውሮፕላኖች መካከል አንዱን አስረከበ።

ፋኦ በኢትዮጵያ የተከሰተውን የአንበጣ  መንጋ ለመከላከል የሚያስችሉ  የሶስት አውሮፕላኖችን በኪራይ አምጥቶ ድጋፍ ያደርጋል።

የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተጠሪ ሚስ ፋቱማ ሰኢድ ዛሬ ለግብርና ሚኒስቴር  የመጀመሪያውን አውሮፕላን ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ቀሪ ሁለት አውሮፕላኖችን በቅርቡ ያስረክባል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ድርጅቱ ሲደግፍ መቆቱን የተናገሩት ሚስስ ፋቱማ፤  በቀጣይም ሶስት የዳሰሳ ስራ የሚያከናውኑ ሄሊኮብተሮችን ጨምሮ መኪኖች፣  የሞተር ሳይክሎችና የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚደርግ ጠቁመዋል፡፡

ለኬሚካል ርጭት የሚያገለግለውን ይኸው አውሮፕላን የተረከቡት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ በበኩላቸው ፋኦ  የኢትዮጵያ  ችግር  በመረዳት ያደረገው ድጋፍ ቀላል አለመሆኑን በመጠቆም ምስጋና  አቅርበዋል፡፡

አሁን ፋኦ በድጋፍ ያቀረባቸው የኪራይ ሶስት አውሮፕላኖች  በአገሪቱ በየአካባቢው የተከሰተውንና በሰው ጉልበት ለመከላከል የማይቻሉትን ለመከላከል የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት መንግስት በኪራይ ካሰማራቸው አራት አውሮፕላኖች ጋር በድምሩ ወደስምንት የሚሆኑ አውሮፕላኖች የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ይሰማራሉ ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ባሰማራቻቸው አውሮፕላኖች በቀን ከ2 ሺህ 200 የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ ስታደርግ እንደነበር ጠቆሙት ዶክተር ካባ፤ የፋኦ ድጋፍ ወጪውን በመቀነስ ረገድ እንደሚረዳ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም