የሊጉ የሁለተኛ ዙር ውድድር ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ የሁለተኛ ዙር ውድድር ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የሁለተኛ ዙር ውድድር ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይቀጥላሉ።
የሊጉ የመጀመሪያ ዙር የውድድር መርሃ ግብር ከሁለት ሳምንታት ዕረፍት ጊዜ በኋላ ነገና ከነገ በስቲያ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራሉ።
በዚህም ሁለት ጨዋታዎች ነገ ፣ቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ እሁድ በክልልና በአዲስ አበባ ስታዲዬሞች ይደረጋሉ።
ነገ ከቀኑ በ9 ሰዓት ፋሲል ከነማ ከአዳማ ከተማ ጨዋታቸውን በጎንደር የሚያደርጉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ቡና ከስሁል ሽረ ከቀኑ በ10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሀዲያ ሆሳዕና ከመቀለ 70 እንደርታ፣ ሲዳማ ቡና ከወላይታ ድቻ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሰበታ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ ከጅማ አባጅፋር እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ እሁድ በተመሳሳይ 9 ሰዓት በክልል ከተሞች የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልቂጤ ከተማ ደግሞ በ10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።
ቅዱስ ጊዮርጊስ የደረጃ ሰንጠረዡን በ28 ነጥብ ሲመራ፤ ፋሲል ከነማ በ26፣ መቀለ 70 እንደርታ በ25 እንዲሁም ሲዳማ ቡና በ24 ነጥብ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ይከተላሉ።
ድሬዳዋ ከነማ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና ሀዲያ ሆሳዕና ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው የሁለተኛ ዙር ውድድራቸውን ይጀምሯሉ።
የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በ14 ጎል ሲመራ፣ ብሩክ በየነ ከሀዋሳ ከነማ በ11 ፣ፍጹም ዓለሙ ከባህር ዳር ከነማ፣ አዲስ ግደይ ከሲዳማ ቡና እንዲሁም ባዬ ገዛኸኝ ከወላይታ ድቻ በእኩል 8 ግቦች ይከተላሉ።