ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድቡን ከዳር ለማድረስ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የደቡብ ክልል አመራሮች ገለጹ

ሀዋሳ የካቲት 27/2012 (ኢዜአ) የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚያስችል መሠረት በመሆኑ ግንባታውን ከዳር ለማድረስ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ በደቡብ ክልል ስልጠና ላይ የቆዩ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ፡፡ 

መካከለኛ አመራሮች በበኩላቸው ስልጠናው የህዝብን ጥያቄ በተሟላ መልኩ ለመመለስና ለውጡን ውጤታማ ለማድረግ እንዳዘጋጃቸው ተናግረዋል።

ከብልጽግና ከፍተኛ  አመራሮች መካከል አቶ ተፈሪ አባተ ለኢዜአ እንዳሉት የኢትዮጵያ ህዝብ ከመነሻው ጀምሮ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በሀሳቡ በመደገፍ ግድቡ አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ አግዟል።

የአሜሪካ መንግስት ጣልቃ በመግባት በድርድሩ ሂደት ላይ ጫና ለማሳደር እያደረገ ያለው ጥረትም ሆነ ግብፅ በግድቡ ላይ እያሳየች ያለችው አቋም አግባብ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በአንፃሩ በኢትዮጵያ በኩል ለድርድር ቅድሚያ በመስጠት በግድቡ ዙሪያ የተያዘው ቁርጠኝነት የተሞላበት አቋም ትክክል በመሆኑ እንደሚደግፉት አመልክተዋል።

"የአሜሪካ መንግስት ጫና ወደ ኋላ የሚጎትተን ሳይሆን አሁን ላይ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ይበልጥ እልህና ወኔ እንድናታጠቅ የሚያደርገን ነው "ብለዋል።

የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማደረስም አንድነታቸውን አጠናክረው ከራሳቸው ጀምረው በመሳተፍ በማስተባበር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ሌላው የፓርቲው  ከፍተኛ  አመራር  ወይዘሮ አምሪያ ሲራጅ በበኩላቸው "በግድቡ ዙሪያ በግብፅና አሜሪካ በኩል እየተንፀባረቀ ያለው አቋም የኢትዮጵያውን በተፈጥር ሀብታቸው የመጠቀም መብት ያላገናዘበ ፤ ዓለም አቀፍ የውሀ አጠቃቀም ስምምነቶችንም የሚጥስ ነው" ብለዋል፡፡

ኢትዮጵዊያን በራሳቸው ሀብት የሚገነቡት ግድብ እንደመሆኑ ቀሪውንም ሥራ ለመጨረስ የሚያስችል የውስጥ አቅም እንዳለ ገልፀው ግንባር ቀደም በመሆን ይህንን የማስተባበርና የመምራት ኃላፊነታቸውን  እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡

 የህዳሴው ግድብ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵዊያን አሻራቸውን ያሳረፉበትና  ሀገራዊ አንድነታቸውን ያሳዩበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ መስፍን ቃሬ ናቸው።

"እንደብፅግና አመራር ግድቡ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት እስኪጀምር ድረስ የሚጠበቅብንን ድጋፍ ሁሉ ማድረግ አለብን "ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ከመካከለኛ አመራሮች መካከል  አቶ መና መኩሪያ  እንዳሉት እየወሰዱት ያለው ስልጠና ለውጡን ውጤታማ ለማድረግ በዕውቀት ለመምራት የሚያስችል ነው።

በስልጠናው ያገኙት ዕውቀት የህዝብን ጥያቄ በተሟላ መልኩ ለመመለስ አቅም የሚገነባ ነው ብለዋል።

አመራሩ እኩል እይታ ኖሮት የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ግንዛቤ ከስልጠናው እንዳገኙ  የተናገሩት በፓርቲው የሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም አምሳሉ ናቸው፡፡

"የነበሩ ያልተገቡ አመለካከቶችን ለመቀየርና ያመለጡ አጋጣሚዎች በአግባቡ በመጠቀም ለመካስ ከፍተኛ መነሳሳትና መነቃቃት የፈጠረ ነው "ብለዋል።

ወይዘሮ ስንታየሁ ተሾመ  በበኩላቸው ሰልጠናውን ከመጀመራቸው በፊት የስም እንጂ ምን ለውጥ ያመጣል ብለው እራሳቸውን ጠይቀው እንደነበር አውስተው ከተከታተሉ በኋላ የለውጥን ምንነትና ውጤት መረዳት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

ላለፉት 11  ቀናት ሲሰጥ የቆየው የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ሁሉም ስልጠና ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

ሪፖርተሮች ሀብታሙና ፋኑኤል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም