የትምህርት ተቋማትን ከኢንዱስትሪዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ተቋማትን ከኢንዱስትሪዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27/2012 (ኢዜአ) የትምህርት ተቋማትን ከኢንዱስትሪዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ከኢንዱስትሪ ጋር የሚያስተሳስር የሁለት ቀን ጉባኤ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።
በጉባኤው ላይ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌን ጨምሮ የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች፣ የኢንዱስትሪ ኃላፊዎች፣ የኩባንያ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ አጋር ድርጅቶች፣ ተመራማሪዎች እና መምህራኖች ተገኝተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በወቅቱ እንዳሉት፤ በጉባኤው የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።
በዚህም የተሻሉ ተሞክሮዎችን ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ መተግበር እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ኢንዱስትሪዎች የተሻለ ምርታማ እንዲሆኑ፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲታገዙና ያለባቸውን የቴክኖሎጂና የክህሎት ክፍተት ለመሙላት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር የማስተሳሰር ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስታውሰዋል።
የትምህርት ተቋማትን ከኢንዱስትሪዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪው ዘመናዊና በምርታማነት ከዓለም አቀፍ አቻ ኢንዱስትሪዎች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆን የትምህርት ተቋማቱ የኢንዱስትሪውን ክፍተት ቀርበው ማወቅ እንዳለባቸው ገልፀዋል።
"በትምህርትና ስልጠና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የትምህርት እና ስልጠና ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ተጨማሪ ኃላፊነት ማስታወስ ከወቅቱ አንጻር ተገቢ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪዎችን ቁልፍ የቴክኖሎጂ እና የክህሎት ክፍተት በመለየት ክፍተቶችን የሚሞላ ሥራ መስራት እንደሚገባም ዶክተር ሳሙኤል አስገንዝበዋል።
ጉባኤው የከፍተኛ ትምህርት እና የኢንዱስትሪ ትስስር ለተሻለ ምሩቅ፣ ችግር ፈች ምርምር ለማካሄድ እና ተስማሚ ቴክኖሎጂ ለማምጣት በሚረዳ ልክ እንዲሆንም ሚኒስቴር ዴኤታው በአጽንኦት ተናግረዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የትምህርት እና ስልጠና ተቋማት ብቁ የሰው ኃይል በማፍራትና ችግር ፈች ምርምሮችን በማካሄድ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉና ግብርናውን የሚያዘምኑ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።