ቀጥታ፡

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ መንግስት የወሰደውን አቋም ከዳር ለማድረስ የህዝብ ድጋፍ ያስፈልጋል

መቀለ  የካቲት 27/2012 (ኢዜአ) በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መንግስት የወሰደውን አቋም ከዳር ለማድረስ የህዝብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ታዋቂው የመልከአ ምድር ምሁር ብርሃኑ በላቸው ገለጹ። 

ምሁሩ አቶ ብርሃኑ በላቸው ለኢዜአ እንደገለጹት የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንደጀመርነው ለመጨረስ ግድ ይለናል ።

መንግስት አሁን የያዘውን አቋም በህዝብ ዘንድ የሚደገፍ በመሆኑ ከጎኑ ልንቆም ይገባል የሚል መልእክትም አስተላልፈዋል ።

የውሃ ሃብት ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጋር በመተባበር የአገርቱን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ ድርድሩን ለማስቀጠል የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ሙሁሩ ጠቁመዋል ።

ድርድሩ ሌላ ሶስትኛ ወገን ሳያስፈልግ በኢትዮጵያ፣በግብጽና ሱዳን መካከል ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

ግብጽ ያቀረበችው የመደራደሪያ ስምምነት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ  ውጭ ተጨማሪ ኢትዮጵያ ሌላ  ግድብ  እንዳትገነባና በአባይ ውሀ እንዳንጠቅም የሚከለክል በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

የአሜሪካ መንግስት በአባይ ተፋሰስ ላይ ጣልቃ መግባቱ አዲስ አለመሆኑን ምሁሩ ተናግረዋል።

በአጼ ሀይለስላሴ ዘመን በ1927 ዓም በጣና መውጫ ላይ ግድብ ለመስራት አቅደው የአሜሪካ ዋይት ኢጅነርንግ የተባለ ተቋም ጥናቱን ካጠናቀቀ  በኋላ ግብፅ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስለነበረች አሜሪካ ለግድቡ ድጋፍ እንዳታደርግ በማግባባት ሳይሰራ መቅረቱን አውስተዋል።

 በ1959 ዓም ተመሳሳይ ተግባር መፈጸምዋን ጠቅሰው ሁሉጊዜ ለግብጽ ያደላ ድጋፍ እንደምታደርግ ይታወቃል ብለዋል።

ምሁሩ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ  ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ያለው እድል፣ የሚያጋጥመው ፈተና፣ የግድቡ ህጋዊነት ፣ተጠቃሚነትና ሌሎች 430 ጽሁፎችን በተለያዩ የውይይት መድረኮች አቅርበዋል።

የህዳሴ ግድብ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች  የአገሪቱ ህዝቦች ጋር በመሆን ትልቅ ዋጋ የከፈለበትና እየከፈለበት የሚገኝ ሃገራዊ ምልክት  መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ገብረሚካኤል መለስ ናቸው።

ህዝቡ  ፕሮጀክት እስኪጠናቀቅ  ድረስ ድጋፉ እንዲቀጥልም  ጥሪ አቅርበዋል ።

አሁን  በፕሮጀክቱ ያጋጠመው የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመመከት የኢትዮጵያ ህዝብ ተሳትፎ የሚያስፈልግበት ወቅት መሆኑን አቶ ገብረሚካኤል ተናግረዋል ።

ህዝቡ በመተባበር ፕሮጀክቱን በፍጥነት እንዲጠናቀቅና የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ገልፀዋል ።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም