የገጠር ፋይናንስ ትኩረት ማጣት ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅፋት ሆኗል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የገጠር ፋይናንስ ትኩረት ማጣት ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅፋት ሆኗል ተባለ
አዲስ አበባ፣የካቲት 27/2012 (ኢዜአ) የገጠር ፋይናንስ ትኩረት ማጣትና ምቹ ሁኔታ አለመፈጠር በገጠር አካባቢ ላለው የሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴ እንቅፋት ሆኗል ተባለ።
በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች እንዲፈቱ የፌዴራልና የክልል መንግስታት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት የሰባት ወራት አፈጻጸም ላይ ተወያይቷል።
በመድረኩ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በሪፖርቱ እንዳመለከተው ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ የግብርና መስክ በሆኑት ሆርቲካልቸርና አነስተኛ መስኖ፣ እንስሳት፣ ዓሣ ማስገር እና ደን ልማት ላይ ብቻ 552 ሺህ 827 የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ እንደገለጹት፤ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ማነቃቃት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአብዛኛው በግብርና ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የገጠር ፋይናንስ ምቹነት ሊታሰብበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የፋይናንስ ስርዓቱ የገጠር ኢኮኖሚውን መሰረት ማድረግ እንዳለበትም ነው የገለጹት።
በገጠር አካባቢዎች አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች የገንዘብ ማስተላለፍና ቁጠባ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውና ለሥራ የሚሆን ብድር አለመስጠታቸው የሥራ ዕድል ፈጠራውን እያገዘ እንዳልሆነ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ከፋይናንስ አቅርቦት በተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና የመስሪያ ቦታ እጥረት ተጨማሪ ችግሮች መሆናቸውን አመልክተዋል።
የአማራ ክልል የቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታደሰ በበኩላቸው አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ያለባቸውን ችግር ለመፍታት ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተለይም በብድር አቅርቦትና የተሰራጨ ብድርን ለማስመለስ አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ለፋይናንስ ተቋማት የተሰጠው ትኩረት ከሚጠበቅባቸው ኃላፊነት አንጻር በቂ እንዳልሆነም ተናግረዋል።
እንደ አቶ ተፈሪ ገለጻ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ተብሎ የሚወጡ ዕቅዶች በበቂ መጠን በስለውና መግባባት ላይ ተደርሶባቸው መሆን ይኖርበታልም።
''የሥራ ዕድል ፈጠራ ያለማሰለስ ክትትልና ድጋፍ የሚፈልግ በመሆኑ የሎጂስቲክ ችግሩ ሊፈታ ይገባል'' ብለዋል።
የደቡብ ክልል የኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማሪያም ተስፋዬ በክልሉ ከዚህ ቀደም የተሰራጨ ብድር በትክክል አለመመለሱ የሥራ ፈጠራ ሂደት ላይ እንቅፋት መፍጠሩን አመልክተዋል።
የልማት ባንክና የካፒታል ዕቃ አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ የሊዝ ማሽን ለማቅረብ መዘግየት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕርግ የትግራይ ክልል የንግድና ኢንዱስቱሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብረሀም ተከስተ በበኩላቸው በክልሉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ቢሆንም ችግሩ እየተባባሰና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል።
የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የብድር አቅም ማነስ የግሉ ዘርፍ ሰፊ የሥራ ዕድል እንዳይፈጥር እያደረገው መሆኑን ተናግረዋል።
"ነባር ኢንተርፕራይዞች ያለባቸውን የመሰረተ ልማትና የግብዓት አቅርቦት ችግር መፍታት ይገባል" ብለዋል።
የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የሶማሌ ክልሎችም ተመሳሳይ የሆነ ፈተና እየገጠማቸው መሆኑን አመልክተዋል።
የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንደገለጹት፤ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመፍታት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚመደበው በጀት ማደግ አለበት።
ወጣቶችን በመስኖ ልማት ለማሰማራት ሁሉም ባለድርሻ አካል መተባበር እንዳለበትም ነው የገለጹት።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው በዘርፉ የታቀደውን ስራ ለማሳካትና ግቡን ለመምታት በውጤታማነት መመራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ያልተቻለባቸውን የመስሪያ ቦታዎች ኃይል ለማይፈልጉ የሥራ መስኮች ማዋል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የህግ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች በአፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ተጠንተው እንዲቀርቡ አስገንዝበዋል።
ለገጠር ፋይናንስ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ መክረው የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያቀርቡም አሳስበዋል።