በስራ ዕድል ፈጠራ ዝቅተኛ ውጤት ላስመዘገቡ መስኮች መፍትሄ እንዲሰጥ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በስራ ዕድል ፈጠራ ዝቅተኛ ውጤት ላስመዘገቡ መስኮች መፍትሄ እንዲሰጥ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2012(ኢዜአ)በስራ ዕድል ፈጠራ ዝቅተኛ ውጤት ላስመዘገቡ መስኮች መፍትሄ እንዲሰጥ ተጠይቋል።
የስራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት የሰባት ወራት ስራ አፈጻጸም ላይ ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ባለፉት ሰባት ወራት ለ1 ነጥብ 67 ሚሊዮን ዜጎች ስራ መፈጠሩን ገልጿል።
ስራ የተፈጠረባቸው አብዛኛዎቹ መስኮች ውጤታማ ቢሆኑም፤ የውጭ አገር የስራ ስምሪትና የኢንፎርሜሽን ኮሙንኬሽን ዘርፎች የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ እንዳልነበሩ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
የፕላንና ልማት ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በበጀት ዓመቱ በስራ ዕድል ፈጠራ ሂደት ዝቅተኛ አፈጻጸም የተመዘገበባቸው መስኮች ተፈትሸው መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂና በውጭ አገር የስራ ስምሪት ላይ ያሉት ክፍተቶች መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።
በውጭ አገር የስራ ስምሪት ከተቀባይ አገሮች ጋር ከሚደረገው ስምምነት በተጨማሪ ለስራ የሚሰማራውን ኃይል ማሰልጠን ተገቢ እንደሆነም ጠቁመዋል።
''ከፍተኛ ክህሎት ያላቸው ሰዎች ላይ ከማተኮር በተጨማሪ በቂ ስልጠና መስጠትም ሊታሰብበት ይገባል'' ብለዋል።
እንደ ማኑፋክቸሪንግና ግብርና ያሉ መስኮች ለዜጎች ስራ ከመፍጠር ባለፈ የምርት አቅርቦትን በማሳደግ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ ስለሚያበረክቱ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።
ወጣቱን የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ በማድረግ የስራ አመለካከትን ለመቀየር መሰራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ የስራ ዕድል ፈጠራን ውጤታማ ለማድረግ የአቅም ክፍተት መፍታትና የግብዓት አቅርቦትን ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል።
ለሴቶች እየተፈጠረ ያለው የስራ ዕድል በቂ ያልሆነበት ምክንያት በጥናት መመለስ እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
''የስራ ፍላጎት ይዘው የሚመጡ ዜጎችን አስተናግዶ ወደ ስራ ማስገባት የሚያስችል አቅም ፈጥሮ መጠበቅ ይገባል'' ብለዋል።
የውጭ ቅጥር በመፈጸም የስራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ ከተለያዩ አገሮች ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ናቸው።
ከነዚህም በመካከለኛው ምስራቅ ከሚገኙ አገሮች ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ በመሰራት ላይ እንደሆነ ጠቁመው ጃፓንና ማልታን ጨምሮ ሠራተኞች ለመቅጠር ፍላጎት ካሳዩ አገሮች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
ከአገሮቹ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚደረገውን ጥረት እየጎተቱ ካሉ ጉዳዮች አንዱ የደመወዝ መነሻ መጠን እንደሆነም አመልክተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዘንድሮው በጀት ዓመት ከዕቅድ ጀምሮ ከክልሎች ጋር በመናበብ የተሻለ ዝግጅት በመደረጉ ውጤት እንደተመዘገበ ገልጸዋል።
ስራውን በተቀናጀ መንገድ በውጤት ተኮር ስርዓት መምራት መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።
የስራ አመራሩ ክትትልና ድጋፍ ማድረጉ ለውጤቱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደነበረው አመልክተው፤ ኮሚሽኑ ያቀረበው ''ለእውነት የተጠጋ'' መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።